ከጥቂት ወራት በፊት በኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት ህብረትና በመሰረት ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ሐሰተኛና አስጸያፊ ተብለው መግለጫ የተሰጠባቸው አዳዲስ አገልጋዮችና አገልግሎቶች እስካሁን ድረስ በስፋት እያነጋገሩ ይገኛሉ። ዶ/ር ወዳጄነህ ሰሞኑን በኤክሶደስ ሾው ላይ በሰጡት ቃለ ምልልስ ምክንያት ይኸው የ“ሐሰተኛ ነብያት” ጉዳይ ትኩስ ትኩረት አግኝቷል። በዚህ ጽሁፍ “ሰው የሚዘራውን ያንኑ ደግሞ ያጭዳል” የሚለውን መጽሃፍ ቅዱሳዊ ህግ መሰረት አድርጌ የዚህን እያነጋገረ ያለ ችግር መንስኤና መፍትሔ ለመመርመር እሞክራለሁ። ዶ/ር ወዳጄነህ ላነሱት “ፕሮቴስታንቱን ምን ነካው?” ላሉት ጥያቄም መልስ አፈላልጋለሁ።

ፍሬ ወይስ አረም?

አረምን አረም የሚያስብለው ዘሪው ያልዘራው መሆኑ ነው። በአብዛኛው በተፈጥሮ የሚገኝ ሲሆን አንዳንዴ ደግሞ ጌታ ኢየሱስ እንዳለው ዘሪው ሳያይና ሳያውቅ በጠላት የሚዘራ ሊሆን ይችላል። አንድ ገበሬ ጤፍ ዘርቶ ስንዴ ቢጠብቅ ቂል ወይም ቀውስ ሊያስብለው ይችላል። እውነትም ቂል ወይም የአእምሮ ጤና የጎደለው ካልሆነ ይህን የሚያደርግ ገበሬ የለም።  እንዲህ ያለው ካልዘራንበትና ያልዘራነውን ለማጨድ የመሞከር ችግር በግብርና ውስጥ የሚታይ አይሁን እንጂ በሌሎች የህይወት መስኮቻችን ሞልቶ የተንሰራፋ ነው። ያላጠናነውን ፈተና ስንወድቅ እንበሳጫለን፣ ያልተለማመድነውን ውድድር ስንሸነፍ እናማርራለን፣ ራሳችን ነጻ አድርገን ተወቃሽ የሚሆንን ሰውና ሰበብ እንፈልጋለን። በመጠጥ ወይም በሲጋራ ወይም በጫት ሱስ የተጠመዱ ወላጆች ልጆቻቸውን በዚያው ሱስ ውስጥ ወድቀው ሲያገኙ አገር ይያዝልን፣ እርሱን ወይም እርሷን ካልገረፍኩ ሞቼ እገኛለሁ ማለትን ከግብዝነት ተርታ የማይመድብ ይልቅ እንደ ተገቢ የወላጅ ባህርይ የሚቀበል ማህበርረሰብ ውስጥ እንደምንኖር ያደግንበትና እየኖርንበት ያለው ባህል ምስክር ነው። የዘሩትን ማጨድ የግብርና ህግ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊውን ህይወት ጨምሮ የሁሉም ህይወት እንቅስቃሴዎች ህግ እንደሆነ መጽሃፍ ቅዱስ ያስተምራል። የዘራውን ሲያጭድ የሚደናገጥ ገበሬ እንደሌ ሁሉ የዘራነውን ስናጭድ ልንደናገጥ፣ ሌሎችን ልንወቅስና ልንቆጣ አይገባንም። ይልቁን ይህ አረም ነው ወይስ ራሴው የዘራሁት ዘር ፍሬ ነው ብለን ልንጠይቅ፣ ከሆነም ፍሬውን ለመቆጣትና ለመግረዝ ከሚወጣው ሃይል ቀንሶ የሚዘሩትን ዘር ዓይነት ማስተካከሉ የተሻለ እርምጃ ነው። ለአረም ያለንን ጥላቻ ወይም አረምን ለማጥፋት ያለንን ቁርጠኝነት እያጣጣልኩ ሳይሆን በአረሙ ላይ ያለን ቁጣ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ለአረሙ ተጠያቂው ማለትም አረሙ እንዲበቅልና እንዲያብብ ምቹ ሁኔታ የፈጠርን እኛው እራሳችን እንሆንን ብለን እንድንጠይቅ፣ ከሆንም ፍርድን ከቤታችን እንድንጀምር ለማበረታታት ነው።

የኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት ህብረት እየተቃወመው ያለው አሁን እየተስፋፋ ላለው የ“ነብያት”፣ የ“ሐዋሪያት” እና የ”እግዚአብሔር ሰው” እንቅስቃሴዎች መነሳትና መስፋፋት ብሎም ተቀባይነት ማግኘት ተጠያቂ ናቸው ብየ የማስባቸውን ልምምዶች ለመግለጽ እሞክራለሁ። ይህን ስል አሁን እየተነሱ ያሉት እነዚህ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ስህተት ናቸው ማለቴ አይደለም። የዚህም ጽሁፍ ዓላማ ስህተት የሆነና ያልሆነውን እንቅስቃሴ ወይም አገልጋይ መለየት አይደለም። እነዚህንም እንቅስቃሴዎች ችግር አለባቸው ብሎ ለማሳመን የተጻፈ ጽሁፍ አይደለም። ምንም ችግር የለባቸውም የሚል አንባቢ ካለ ይህ ጽሁፍ ብዙም የሚጠቅመው አይመስለኝም። ችግሮች አሉ ብሎ ለሚያምን አንባቢ ግን ለችግሮቹ ተጠያቂው ማነው? መፍትሔውስ ምንድን ነው? የሚለውን የሚያወያይ ጽሁፍ ነው። መቼም ማናችንም ብንሆን ከመጽሃፍ ቅዱስ በእጅጉ ያፈነገጡ ልምምዶችና ትምህርቶችን በአካል ይሁን በሚዲያዎች በተካፈልናቸው አገልግሎቶች ሳንታዘብ አልቀረንም። እነዚህንም ልምምዶች አስመልክቶ በአብያተ ክርስቲያናቱ ይሁን እኔ በምገለገልበት የሎስ አንጀለስ ቤተ ክርስቲያን ከተላለፉት መግለጫዎች ጋር በአመዛኙ እስማማለሁ። ይሁን እንጂ ለእነዚህ መረን ለወጡ ልምምዶችና ትምህርቶች ተጠያቂው እነዚህ “አዳዲስ” አገልጋዮች ብቻ ሳይሆኑ በህብረቱ የታቀፉ “ነባር” አብያተ ክርስቲያናትና አገልጋዮችም ጭምር ናቸው ብየ ለመሞገት እፈልጋለሁ። ከዚህ በታች የምዘረዝራቸው ችግሮች በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት የሚታዩ ችግሮች ላይሆኑ ይችላሉ። አንዳንዶቹ የአንድ ወይም የሁለት ቤተ ክርስቲያን ችግሮች ሊሆኑ ይችላሉ፣ ሌሎች ደግሞ በብዙ አብያተ ክርስቲያናት የተስፋፉ ሊሆኑ ይችላሉ። እንዲሁም በአንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ ምዕመናን ወይም መሪዎች ሁሉ ተጥያቂዎች ናቸው ማለት አይደለም። በአንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለ ችግር ምናልባት የአብዛኛው ምዕመን ወይም መሪ ችግር ሊሆን ይችላል፣ ይሁን እንጂ በዚያ ቤተ ክርስቲያን ያለ እያንዳንዱ ምዕመን ወይም መሪ የዛ ችግር ተጠቂ ነው ማለት አይደለም። አሁን እየታየ ያለው ችግር ሊያስገርመን የሚገባ ባዕድ አረም አይደለም የሚለውን ሳሳይ ለእነዚህ “አዳዲስ” ልምምዶች መነሳትና መስፋፈት ምቹ ሁኔታን (ባህልን) የፈጠሩ በእኛው “ትክክለኛ” ልምምድና ትምህርት አለን በምንለው የሚታዩ ጉድለቶችን በመንቀስ ነው። ዶ/ር ወዳጄነህም “የእግዚአብሔር ህዝብ እንዴት አይለይም?” ላሉት ጥያቄ፣ ለእኔ ቢያንስ ግማሹ መልስ፦ አብዛኛው አማኝ መለየት የሚችልበት የዳበረ ልማድና ባህል ስሌለለው የሚለው ነው። እንዲያውም ያሉት ሃይማኖታዊ ባህሎችና ልማዶች ለዚህ ዓይነት መስመር ለሳቱ እንቅስቃሴዎች መነሳትና መስፋፋት ምቹ ሁኔታ ፈጣሪዎች ናቸው።

ተጠያቂ ባህሎቻችን/ልማዶቻችን

1. የጥራዝ ነጠቅ ባህል

ዛሬ ዛሬ ከሚጠቀሰው ጥቅስ አውድ ጋር የሚጣረስ አተረጓጎም መከተል እንደመገለጥ ሆኖ እየቀረበ ሳይ በብዙ “ነባር” አብያተክርስቲያናት አገልጋዮች ላይ ይታይ የነበረውንና አሁንም ያለውን ጥራዝ ነጠቅ አተረጓጎም ለብዙ ዓመታት ቸል ማለታችንን አስባለሁ። ኢትዮጵያ በነበርኩ ጊዜ የትኛውም ጉባኤ ስካፈል፣ አውዱን ግንዛቤ ውስጥ ያላስገባ አፈታትን ቢያንስ አንድ ጊዜ ሳልታዘብ የተካፈልኳቸው ፕሮግራሞች በጣም ጥቂቶች ናቸው። አተረጓጎማቸው አውዱን የተከተለ ባይሆንም ጥቅሱን ተንተርሰው የሚሉት ነገር ተቀባይነት ካለው የክርስትና አስተምህሮ ጋር ባብዛኛው የተስማማ ስለሆነ እንዲህ ያለውን ችግር ቸል ብለን ኖረናል። ይህ ባህል ግን ሌሎችም ይህን ጥራዝ ነጠቅ አተረጓጎምን ወደ ጽንፍ በመውሰድ ከአውዱ ጋር የማይሄድ አተረጓጎምን እንደ መገለጥ እያቀረቡ ስህተትን ያለምንም ፍርሃት እንዲያስተምሩ የልብ ልብ የሰጠ ሆኗል። ከዚህ የተነሳ አማኙ አውዱን የሳተውን አተረጓጎም እንኳን ራሱ ሊመረምር አይደለም ከዚህ ቀደም ያልተለማመደው በመሆኑ አውድና ሌሎች የስነ አፈታት መመሪያዎች ሲነሱ፣ አዳዲሶችን አገልጋዮች ለመቃወም ሆን ተብሎ እንደ ተጠነሰሰ ሴራ ማሰቡ አልቀረም። አገር ውስጥ ያሉ ይሁን በውጭ አገር ያሉ “ነባር”ና “ትክክለኛ” አብያተ ክርስቲያናት ነን የምንል ሁሉ መጀመሪያ ራሳችንን በዚህ ጉዳይ ለማጥራት መወሰን እንዳለብን ይሰማኛል።

በዚህ ችግር ዙሪያ ብዙ ስለተባለና እየተባለ ስላለ፣ ነገር ላለመደጋገም ስል በአጭር ቋጭቸው ወደ ሌሎች ትኩረት ያነሳቸው ናቸው ብየ ወደ ማስባቸው 4 ጉዳዮች ልሂድ፦

2. ጠያቂነትንና ማረጋገጫ ፈላጊነትን እንደ እምነት ማጣት ምልክት አድርጎ የማየት ባህል

ዛሬ ከመስመር የወጡ የነብያትና የ“እግዚአብሔር ሰው” እንቅስቃሴዎች ሲበራከቱ፣ “እስኪ የታለ ፈውሱ?” ለማለት እንፈልጋለን፣ ለምስክርነት በየሚዲያው የሚቀርቡትን መስካሪዎች “የታለ ማስረጃችሁ?” ማለት እንፈልጋለን። ግን የት ያስለመድነውን ባህል? ማስረጃ እና የሚታይ ግልጽ ለውጥ ሳይኖር ከሙሉ ወንጌል ወይም ቃል ህይዎት ወይም መካነ ኢየሱስ ወይም መሰረተ ክርስቶስ… የመጣው አገልጋይ “ተፈውሰሃል”፣ “ተፈውሰሻል” ሲል እልል እያልን ለ“መጤው” አገልጋይና ቤተ ክርስቲያን ማስረጃ ካላሳያችሁ ብሎ መሞገት ለትዝብት እንጂ ለለውጥ አያበቃንም። ነባሮቹም ይሁኑ አዳዲሶቹ የፈውስ አገልጋዮች ትኩረታቸው ሆነ መገለጣቸው በ“ውስጥ ደዌ” ላይ ያተኮረ ስለሆነ፣ እውነት ፈውሱ ይሁን አይሁን፣ የመጣው መገለጥ ይፈጸም አይፈጸም ለማወቅ በጣም አስቸጋሪ ነው። በዚህ ላይ “እውነት ተፈውሷል?” ብሎ መጠየቅን የሚያወግዝ ባህል ስር ከመስደዱ የተነሳ፣ ፈውሶች ገና በሃኪም ወይም በጋህዱ ዓለም በሚታይ ለወጥ ሳይረጋገጡ ለምስክርነት ይበቃሉ። በል በይ፣ አይዞህ አይዞሽ ተብሎ ገና ፈውሱ በሰውነታቸው ሳይታወቃቸው ተመልካቹም  ሳያሳምነው ለምስክርነት መድረክ ላይ ጉብ ይባላል። ቤተ ክርስቲያን ነባር ወይም አዲስ፣ ታዋቂ ወይም እንድግዳ አገልጋይ ሳትል እንዲህ ያሉ የፈውስና የምስክርነት ልምምዶችን ቀደም ብላ ብታርም፣ ውሎ አድሮ ታይቶ ወይም በሃኪም ተረጋግጦ ካልሆነ ለምስክርነት መቆም አይቻልም የሚል ባህል ቢኖራትና ባልተፈጸሙ የፈውስ ትንቢቶች ተንባዮችን ተጠያቂ የምታደርግበት ባህል ቢኖራት ኖሮ፣ ዛሬ በየቦታው እየፈሉ ያሉ ሐሰተኛ የፈውስ አገልጋዮችን “ተቆርቋሪና አስተዋይ” መሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ህዝቡም በቀላሉ ይለያቸው፣ ያገላቸው፣ ያጠወልጋቸው ነበር ብየ አስባለሁ። እምነት የእግዚአብሔርን ቃል ማመን እንጂ፣ ከእግዚአብሔር ይሁን አይሁን ገና ያልተረጋገጠን የ“ነብይ” ቃል ማመን አይደለም። እምነት በእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ላይ ሳይጠራጠሩ መደገፍ እንጂ አይኑን አፍጥጦ የተቀመጠ እውነታን መካድ አይደለም። ከፈውስ በኋላ “ራስህን ለካህን አሳይ” ብሎ መፈወሱን በካህን እንዲረጋገጥለት ከላከው፣ የአይነ ስውሩ አይን አጥርቶ እስኪያይ እያጣራ ከጸለየው ከጌታችን ከክርስቶስ ልንማር፣ ፈውስ መሆን አለመሆኑን ማጣራት የእምነት ማጣት ምልክት አለመሆኑን አማኙ እንዲያውቅ ብሎም በግሉና በጉባኤም እንዲለማማድ መንገድ ማሳየት የ“ነባር” አብያተ ክርስቲያናትና አገልጋዮች ሃላፊነት ነው። ያየነውን የእግዚአብሔር ስራ አለመመስከር በእግዚአብሔር ፊት የሚያስጠይቀውን ያህል ለእግዚአብሔር ሐሰተኛ ምስክሮች መሆንም ያስጠይቃል። ሐዋርያት በሰጡት የአይን ምስክርነት የተመሰረተ እምነት (ሐይማኖት) የምንከተል እንደመሆናችን መጠን ጥንቃቄ ለሞላበትና እውነተኛ ለሆነ ምስክርነት የምንሰጠው ቦታ ከፍተኛ ሊሆን ይገባዋል። በሆነ ባልሆነው “መስክር”፣ “መስክሪ” እየተባባልን ምስክርነት ያለውን ትልቅ ቦታ ማራከስ ከእኛ የሚጠበቅ አይደለም።

3. ተጠያቂነትን የሚያዳክም የይሉኝተኝነት ባህል

አገልጋዩ ሰውን እየገፋ ሲጥል ሰው ምን ይለኛል ያለማለት ባህል፣ ባንጻሩ የተገልጋዩ ተገፍቶ ሲወድቅ በመንፈስ ቅዱስ አስመስሎ ዝም ማለቱ፣ የገፋው ሳይሳቀቅ የተገፋው መሳቀቁ፤ ምንም ለውጥ ሳይኖር አገልጋዩ “አሁንስ እንዴት ነው?” እያለ ሲያሳቅቅ፣ ተገልጋዩ በይሉኝታ “አሁን ትንሽ ትንሽ ደህና ነኝ” ለማለት ሲገደድ፣ ለፈውስ እጅግ የጓጓው ጉባኤ ደግሞ ለፈውሱ መከናወን ቅንጣት ታክል ማስረጃ ሳይኖር በእልልታና በጭብጨባ ማጀቡ። እንዲህ ያለው ባህል፣ አገልጋዩ ያለምንም ተጠያቂነት የፈለገውን ብሎና አድርጎ እንዲኖር ሲያበረታታ፣ ተገልጋዩ ደግሞ የመጠየቅና የመፈተን ተፈጥሮው እየተሸረሸረ፣ ምንም ቢሉት አሜን የሚል፣ ምንም ቢያደርጉት በጸጋ የሚቀበል ሆኗል። እንዲህ ያለው ሁኔታ የወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናቱ ህብረት በምንም መልኩ ባልነቀፋቸው ሰፊ ተቀባይነታ ባላቸው አገልጋዮች ዘንድ በሰፊው የሚታይ እንደሆነ ማናችንም የምንክደው አይመስለኝም። እኔ በምገለገልባቸው አጥቢያዎች በትኩረት በተካፈልኳቸው ኮንፈረንሶች እንዲህ ያለውን ልምምድ በሚገባ አይቻለሁ። ሰዎችን ድንገት ሳያስቡት በመግፋት፣ አንገታቸውን በመቆልመም፣ ከሚችሉት በላይ በሆነ ጉልበት እጅን በመጫን፣ በመንፈስ ቅዱስ አስመስለው ሰዎችን የሚጥሉ ብዙ “ነባር” አገልጋዮችን ታዝቤአለሁ። ተገልጋዩም ካልወደቀ ከሰው ተለይቶ “መንፈስ ቅዱስ ያልነካው” መባልን ከመፍራት የተነሳ ራሱን በመጣል አገልጋዩን ይተባበራል። በእነዚህ ኮንፈረንሶች የተጸለየለት፣ እንደተፈወሰ የተነገረው ወይም ማረጋገጫ እንዲሆነው ልዩ ምልክት የተሰጠው በጣም ብዙ ሰው ቢኖርም፣ እኔ እስከማውቀው አንድም ለምስርነት በሚበቃ መልኩ የተረጋገጠ ፈውስ አላየሁም። አገልጋዩ ተፈውሳችኋል ብሎ ከማወጁ ባለፈ ሰዎቹ ካለባቸው የሚታይ ደዌ ተፈውሰውም ይሁን፣ ከማይታይ ደዌያቸው ለመፈወሳቸው ማረጋገጫ ይዘው ሲመሰክሩ አላየሁም። ይህን ስል ፈጽሞ ፈውስ አይቼ አላውቅም ማለቴ እንዳልሆነ ማሳሰብ እወዳለሁ። እየሰጠሁት ያለው አስተያየት ባለፈው አንድ አመት ተኩል በአካል ተገኝቼ የተካፈልኩባቸውን ኮንፈረንሶች የተመለከተ ነው። እነዚህን የመሰሉ ስር የሰደዱ ችግሮች ቢታዩም እነዚህን ኮንፈረንሶችን ያዘጋጁ አጥቢያዎች አንድም ቀን በቤተ ክርስቲያን ደረጃ እንዲህ ያለውን ሰውን ገፍቶ ወይም አሳቆ የመጣል ይሁን የተገባው የፈውስ ተስፋ ፍጻሜ የማጣትን ጉዳይ በቤተ ክርስቲያን ደረጃ ለተግሳጽ ይሁን ለአስተያየት ሲያነሱ አላየሁም።  በእኔ አመላካከት እንዲህ ያለው ባህል አሁን እየተነሱ ላሉ “ሐሰተኛ” እየተባሉ ለሚነቀፉት አገልጋዮች መብቀል ብሎም ማበብ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ረገድ ከዋነኞቹ ተጠያቂዎች አንዱ ነው። ታዲያ እንዲህ ያለውን እንደ ግንድና ስር ያለ ባህል ወደጎን ትቶ፣ ባህሉ እንደ ቅርንጫፍ ያበቀላቸውን “ሐሰተኛ” አገልጋዮችን ለመግረዝ መሞከር ከንቱ ልፋት ነው፣ ነገ ሌላ ቅርንጫፍ በሌላ አቅጣጫ ብቅ ማለቱ አይቀርምና። መሪዎች ገፍተው የሚጥሉ አገልጋዩችን ማረም ይኖርባቸዋል፣ ተገልጋዩም ይሉኝታና ሀሰተኛ ምስክርነት በእግዚአብሔር መንግስት ድርሻ የሌላቸው መሆኑን ተረድቶ የእንደዚህ ዓይነቱ ልማድ ተባባሪ መሆኑን ማቆም አለበት ብየ አምናለሁ። እንዲህ ያለ ጥንቃቄና ተጠያቂነት ያለበትን ባህል አዳዲሶቹ ብቻ እንዲያሳዩ ከመጠበቅ አልፈን እኛ “ነባሮቹም” ስራ ላይ ብናውለው የረጅም ጊዜ ለውጡ ከአውጋዥ መግለጫ የተሻለ እንደሚሆን አስባለሁ።

4. ትንቢትን ያለመፈተን ባህል

ከሞላ ጎደል በቤት ክርስቲያን የሚሰጡ ትምህርቶችን የመፈተንና የመተቸት ባህል አለን። አማኞች በግላቸው ይሁን ከጓደኞቻቸው ጋር ሆነው የተማሩትን ትምህርት ወይም የተሰበኩትን ስብከት ይወያያሉ፣ ይተቻሉ። ትክክለኛ ያለሆኑ ትምህርቶች ሲሰጡም መሪዎች ትምህርቱን ያስተማሩ አገልጋዮችን ጠርተው ያነጋግራሉ፣ ማስተካከያም ይሰጣሉ። የትምህርት ችግር ያለባቸውም አገልጋዮች መድረክ እንዳያገኙ ጥንቃቄ ይደረጋል። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው ተገቢ ባህል ወደ ትንቢት አገልግሎት ዘውር ስንል ደብዛው አይገኝም። ትንቢትን እንድንመረምር፣ እንድንለይ፣ እንድንፈትን መጽሃፍ ቅዱስ ያበረታታናል። ነገር ግን ስንቱ ተንባይ የፈለገውን ተንብዮ ያለምንም ተጠያቂነት ተቀምጧል፥ አገልግሎቱንም ቀጥሏል? ቤተ ክርስቲያን የስንቱን ትንቢት ተፈጻሚነት ትከታተላለች? ከእግዚአብሔር ይሁን አይሁን ትመረምራለች? በወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናቱ ህብረት ውስጥ ያሉ አገልጋዮች የተናገሯቸው ግን ያልተፈጸሙ ብዙ ትንቢቶች አሉ። ብዙ አገልጋዮች ለአገልግሎት ኮንፈረንሶች በተጋበዙ ቁጥር በሄዱበት ከተማና ቤተ ክርስቲያን ላይ የትንቢት ናዳ ማውረድ የተለመደ ባህል ነው። ተወልጄ ባደኩበት የባህር ዳር ከተማ ብዙ ኮንፈረንሶች ላይ በከተማዋና በቤተ ክርስቲያኗ “ዛሬ”፣ “በዚህ ዓመት”፣ “በዚህ ወር” እየተባሉ የተነገሩ ለቁጥር የሚያዳግቱ የጅምላ ትንቢቶችን ሰምቻለሁ፣ እኔ እስከማውቀው አብዛኞቹ ትንቢቶች ሲፈጸሙ አላየሁም። “በህይወት ትኖራለህ፣ የእግዚአብሔርን ማዳን ታወራለህ”፣ “ውጭ ሃገር ለጉብኝት እንጂ ለህክምና አትሔድም” እየተባለ በ“ነባር” አገልጋዮች የተነገረለት ስንቱ አልቋል። በወንጌል ስራ አለምን እንደሚዞር ትንቢት ያልተነገረው ሰው ያለ አይመስለኝም፣  የስንቱ ግን ተፈጽሟል? ደብተር ሙሉ “የተስፋ ቃላቸውን” እንደተሸከሙ ያንቀላፉትንና የመቃብር አፋፍ ላይ የደረሱትን ቤት ይቁጠራቸው። “ነባር” ምዕመናንና መሪዎች ይህን ችላ ስንል ከርመን ቀልባችን ስላልወደዳቸው ብቻ በሚመስል ምክንያት በእነዚህ አዳዲስ “ነብያት” ላይ የውግዘት መዓት ማዝነብ ምን ይሉታል? ደግሞስ ዛሬ በየቤተ ክርስቲያኑ የሚነገረው የባገኝ ባጣ (የግምት) ትንቢት መቼ ነው እርምት የሚሰጠው? “እንደዚህ የሆናችሁ 10 ወይም 20 ሰዎች አላችሁ፣ ዛሬ እግዚአብሔር ፈውሷችኋል” ወይም “ዛሬ እግዚአብሔር ከእናንተ ላይ አንስቶታል” የሚሉ ትንቢቶችን የማረምና የመፈተን ባህል ቤተ ክርስቲያን ልታዳብር ይገባታል። እኔ አሁን በምኖርበት አገር በአሜሪካ አብዛኛው ሰው በእዳ የሚኖር ነው፣ ቢያንስ መኪናው ወይም ቤቱ በእዳ የተገዛ ነው። ታዲያ አንዳንድ አገልጋዮች “የኔ ወንድም እዳ እንዳለብህ የጌታ መንፈስ ያሳየኛል” ወይም “በዚህ ጉባኤ እዳ ያለባችሁ 50 ሰዎች አላችሁ፣ እዳችሁን የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ‘እኔ ከፍየዋለሁ’ ይላችኋል” ሲሉ ስሰማ በአንድ በኩል አገር ያወቀውን ጸሃይ የሞቀውን እውነታ ትንቢት ብለው ሲናገሩ አለማፈራቸው፣ በሌላ በኩል ደግሞ ማንም እዳው መከፈል አለመከፈሉን ተከታትሎ ሊጠይቃቸው እንደማይችል ስለሚያውቁት ትንቢት ተናጋሪዎቹ የሚያሳዩት ድፍረት ያስገርመኛል። እንዲህ ያለውን ትንቢት ጥያቄ ሳታነሳ ለረጅም ዘመን የምታስተናግድ ቤተ ክርስቲያን ምዕመኗን ለተኩላዎች እያመቻቸች እንደሆነ ይሰማኛል።  ሌላው የትንቢት ዓይነት ደግሞ አንዳንድ ሰዎች ድንገት ከጉባኤ ብድግ ብለው ከብሉይ ኪዳን በቀጥታ የተገለበጠ የሚመስል “ህዝቤ ሆይ እኔን ብትሰማ፣ ከጥፋትህ ብትመለስ እኔ እባርክሃለሁ፣ ጠላቶችህን አጠፋለሁ ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር”፣ “ህዝቤ ሆይ አንተ ፊቴን ብትፈልግ፣ ከክፉ መንገድህ ብትመለስ” እያሉ የሚናገሩት ዓይነት ነው። እነዚህ ዓይነት ትንቢት ተናጋሪዎችን “ትንቢታችሁ የሚመለከተውን ግለሰብ ወይም ቡድን አጣርታችሁ፣ ከየትና ወዴት እንደሚመለሱ እንዲሁም የሚያገኙት የበረከት ዓይነት ምን እንደሆነ አጣርታችሁ ካልመጣችሁ ለመፈተን ስለማይመቸን በጉባኤ አትናገሩ” ልንላቸው ይገባል ብየ አስባለሁ። እንዲህ ያሉትን ለብዙ አስርት ዓመታት መታገስ ግን አወናባጅ ወይም ጭልጥ ያለ ስህተት የሚናገሩ ተንባዮች ሲመጡ አማኙን ለማስጠንቀቅ የሚያስችል አቅምም ይሁን ተሰሚነት አይኖረንም። መፈጸም አለመፈጸማቸውን ለማረጋገጥ የማይቻሉ ለያዥ ለገናዥ የሚያስቸግሩ ትንቢቶችን መናገር የጸጋ ስጦታዎችን እንለማመዳለን በሚሉ አብያተክርስቲያናት ለብዙ ዘመን እየታየ ያለ ችግር ነው። መገለጥ ተናጋሪ የሚያገለግልበት ጉባኤ ውስጥ ስንቶቻችን ነን “ስላንተ/ቺ የማስባትን ሃሳብ እኔ አውቃለሁ”፣ ወይም “የኔ ወንድም እግዚአብሄር ችግርህን ተመልካቻለሁ፣ ነገር ግን የሚያስጨንቅህን ሁሉ በእኔ ላይ ጣል ይልሃል” የሚል ትንቢት ያልሰማን? እነዚህን የመሰሉ አጠቃላይ ምክር አይሏቸው ወይም ትንቢት፣ ለፍተሻ የማይመቹ፣ መሬት ያልያዙ፣ እውነት ወይም ሃሰት ብሎ ለመፈረጅ የማይቻሉ ምንም ዓይነት ጊዜ ይሁን ቅድም ሁኔታ ያላስቀመጡ ትንቢቶች ሞልተዋል። እነዚህ ጉዳት የለሽ የሚመስሉ ልምምዶችን ችላ ብሎ ማለፍ፣ ከመስመር የወጡ፣ ውጤታቸው አስከፊ የሆኑ ትንቢቶችን ሰዎች ያለምንም ፍርሃት እንዲናገሩ ያደፋፍራል፣ ቁጥራቸውም እንዲበራከት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፣ አማኙም በደህና ጊዜ ባለመለማመዱ ለመፈተን ይሁን ለመቃዎም አቅሙም ይሁን ልምዱ የሌለው ስለሚሆን ለበዝባዦች በቀላሉ ተላልፎ ይሰጣል።

የተለመዱ ምላሾች

አንዳንድ ሰዎች ላልተፈጸሙ ትንቢቶችና ፈውሶች ምክንያቱ ትንቢቱ የተነገረላቸው ሰዎች እምነት ማጣት ወይም አለመታዘዝ ወይም በቂ ዝግጅት አለማድረጋቸው እንደሆነ አድርገው ይከራከራሉ። ከእምነት መድከም ወይም አለመታዘዝ ሳይፈጸሙ የሚቀሩ ትንቢቶች እንዳሉ ምንም አጠያያቂ አይደለም። በእንዲህ ሁኔታ ሳይፈጸሙ የሚቀሩ ትንቢቶች ግን ከመጽሃፍ ቅዱስ እንደምናየው ቁጥራቸው አነስተኛ ሊሆን ይገባዋል እንጂ አሁን እንደምናየው አብዛኛው ትንቢት ሲሆን ግን ቆም ብሎ መጠየቅ በጣም አስፈላጊ ነው። በመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ ለተፈጻሚነት የሰሚውን እምነት ወይም ዝግጀት የማይፈልጉ ብዙ አይነት ትንቢቶች መኖራቸውንም ማሰብ ይኖርብናል። አለበለዚያ ሰው የፈለገውን ትንቢት እየተናገረ ሳይፈጸም ሲቀር እምነት ማጣትንና አለመታዘዝን ሰበብ ማድረግ ቀላል ነው። እንደዚህ ያለውን ደካማ ምክንያት ለነባር አገልጋዮች የምንቀበል ከሆነ ግን ተመሳሳይ ምክንያት እያቀረቡ ያሉትን አዲሶችን አገልጋዮች የምንቃወምበት አንደበት አይኖረንም። የምክንያቶችን ደካማነት በአጭሩ ለማሳየት አንዳንድ ሃሳቦችን ማንሳት ይችላል። ለምሳሌ ልጅ ያጡ ባለትዳሮች “ጌታ የዛሬ ዓመት ልጅ እሰጣችኋለሁ ይላል” ከተባሉ ከአንድ ዓመት በኋላ ተስፋ የተገባው ልጅ ሲቀር ስላላመኑ ነው የሚለው ምክንያት የሚያስኬድ አይሆንም። ወይ ሲጀምር ትንቢት ተናጋሪው “ካመናችሁ” የሚል ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጥ አለበት ወይ ተጠያቂ ለመሆን ፈቃደኛ መሆን አለበት። “ካመናችሁ” የሚል ቅድመ ሁኔታ የሚቀመጥ ከሆነ ደግሞ ትንቢቱን ትንቢት ማለት ይከብዳል፣ ትንቢት ከተባለም አስፈላጊነቱ አጠያያቂ ነው። ነብሰ ጡር የሆነችን ሴት “ሲሆን ሲሆን ወንድ፣ ካልሆነ ደግም ሴት ትወልጃለሽ” ብሎ ከመንተንበይ ያለፈ ትርጉም የሚኖረው አይመስለኝም። እንደዚህ እውነት ይሁን ውሸት መሆኑን ማረጋገጥ የሚያስቸግር ትንቢት ተገቢ ስላልሆነ ነው በመጽሃፍ ቅዱስ እንዲህ ያለ ቅደመ ሁኔታ ያዘለ ትምህርት፣ ትዕዛዝ ወይም ማስተንቀቂያ እንጂ ትንቢት እምብዛም የማናገኘው። ሌላው “ተፈውሰሃል” ካሉ በኋላ “እምነት ስለሌለው ነው እንጂ ተፈውሶ ነበር” የሚለው በመጽሃፍ ቅዱስ የተዘግቡትን ፈውሶች ለሚያነብ ሰው እንግዳ ነገር ነው። እየተፈጠረ ያለውን ችግር በማጤን ብዙ ትንቢት ተቀባዮች የእምነት እጥረት እንደሌለባቸው ማሳየት ይችላል። ለምሳሌ ያህል፦ ስላመኑ አይደለም መድሃኒታቸውን እየተው፣ ለህክምና ሌላ አገር መሄዳቸውን እየተው፣ ሃኪም የከለከላቸውን ምግብ እየበሉ፣ ወ.ዘ.ተ. እየባሰባቸውና እየሞቱ ያሉት? ደግሞስ ሳያምኑ አገር አቋርጠው፣ ገንዘብ አውጥተው፣ ጊዜያቸውን አቃጥለው፣ የ“እግዚአብሔርን ሰው” ተለማምጠውና ከነችግራቸው በቴሌቪዥን መስኮት ለህዝብ መቅረባቸውን ታግሰው ይቀመጡ ነበር? እንዴው “እምነት የላቸውም!” ብለን ሙጥኝ ካልን ደግሞ በሌላ መልክ እንየው፦ እምነት ለፈውሱ አስፈላጊ ከሆነና ትንቢት የሚነገርለት ሰው እምነት ከሌለው ወይም ከጎደለው፣ ያ ሰው መጀመሪያውኑም አልተፈወሰም ማለት አይደለም? ካልተፈወሰ ደግሞ “ተፈውሰሃል” የሚለው ትንቢት ሲጀመር ስህተት ነው ማለት አይደለም? ኢየሱስ “ልጅህ ተፈውሷል” ብሎ ያሰናበተው አባት ቤቱ ሲሄድ ሞቶ ቢያገኘውና ወደ ኢየሱስ ተመልሶ ሲጠይቅ፣ ኢየሱስ “አዎ ልጅህ ተፈውሶ ነበር፣ በመንገድ ግን ስትመለስ የሰዎችን ወሬ እየሰማህ እምነትህ ስለቀነሰ በሽታው ተመልሶበት ገደለው” የሚል ምላሽ ቢሰጠው እንደማለት ነው። እምነት ከሌለ መጀመሪያውኑ ፈውስ የለም ከሌለም “ተፈውሰሃል” የሚል “መገለጥ” ሊኖር አይገባውም። በተጨማሪም በመጽሃፍ ቅዱስ በአብዛኛው እንደምናየው ሰው ሲፈወስ ምስክርነቱን የሚሰጠው ራሱ ወይም ለውጡን የሚያዩ በዙሪያው ያሉ ሰዎች እንጂ የፈውስ ስጦታ አለኝ የሚለው ሰው አይደለም።  የሚታይ ፈውስ ማድረግ የተሳናቸው ሰዎች መብዛት ይሆን ፈውስ ገሃዳዊ ለውጥ ከመሆን ወጥቶ “መገለጥ” ጎራ ውስጥ የገባው?  የሰውን እምነት ለክቶ ማነስ መብዛቱን ሊናገር የሚችል ሰው ስለሌለ፣ እምነት ማጣትን ለትንቢት (ፈውስ) አለመፈጸም እንደሰበብ ማቅረብ በጣም ቀላል ነው። እንዲህ ያለውን ሰበብ አገልጋዮች ሲጠቀሙ ሁለት ሶስት ጊዜ መታገስ ተገቢ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ይህን የመሰለ ሰበብ ሰለባ የሚሆኑ ትንቢቶችንንና መገለጦችን መናገር ልምዳቸው አድርገው የያዙ “ነብያት”ን መታገስ ቂልነት እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም። እንዲህ ቂልነትን ሲያነግሱ ከከረሙ በኋላ እንዳሁኑ ችግሩ እየከፋ ሲሄድ ህዝቡን እናስጠነቅቃለን ብንልም የሚሰማን አይኖርም፣ መተማመን በነበረ ጊዜ ያላስቀመጥነውን መለኪያ መተማመን ከጠፋ በኋላ ልንጠቀምበት ያስቸግራል።

5. እውቀትን፣ ምርምርንና ሳይንስን እንደ እግዚአብሔርና መጽሃፍ ቅዱስ ጠላት የማየትና፣ ችግሮችን ሁሉ በተዓምር ለምፍታት/ለማስፈታት የመሞከር ባህል

ሌላው አሁን አሁን እያሳሰበ ለመጣው አዲስ እንቅስቃሴ መፈጠርና ማደግ ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ ያለው ባህል ይህ ትምህርትን፣ ምርምርን፣ እውቀትንና ሳይንስን የማጣጣል ብሎም የእግዚአብሔር ስራና ቃል ተቀናቃኝ እንደሆኑ አድርጎ የማየት ባህል ነው። “ስለተመራመርክ አይደለም”፣ “ስለተማርክ አይደለም”፣ “በአእምሮ አይደለም” የሚለውን አባባል ከብዙ ሰባኪዎች መስማት እንግዳ ነገር አይደለም። ለምሳሌ የአንድን ሰው ስኬት አይታችሁ ተሞክሮውን እንዲያካፍላችሁ ብትጠይቁ “ጌታ እኮ ነው” ከማለት ያለፈ፣ ወይም በሆነ ጉዳይ ጥያቄ ኖሯችሁ ብትጠይቁ፣ “ብቻ አንተ ጸልይ” የሚለውን መልስ እንጂ ምክንያታዊነትን መሰረት ያደረገ ምክር ከእኛ “ከነባሩ” ወንጌላዊያን አማኞች የማግኘታችሁ እድል በእጅጉ የጠበበ ነው። መድረክ ላይ የቆመው ሰው የወደደውን ከተናገረ በኋላ “የኔ ወንድም ይህ በሰው አእምሮ የሚመረመር አይደለም” በማለት ራሱን ከተጠያቂነት ለማዳን የአድማጩን የመፈተንና የመመርመር ትጥቅ ማስፈታት የተለመደ ስልት ነው። በተጨማሪም ሳይንስንና ሳይንቲስቶችን እንደ መጽሃፍ ቅዱስ ጠላት በማቅረብ ነጥብ ማስቆጠር ሌላው ችግር ነው። ሳይንስንና ምክንያታዊነትን የእምነት ጠላት አድረገው የሚያዩና የሚያስተምሩ ሳይንቲስቶችን ጨምሮ ብዙ ሰዎች እንዳሉ የሚካድ አይደለም። እኛ አማኞች ግን ሳይንስና ክርስትና የሚያገናኛቸውን ይሁን የሚያጣላቸውን ጉዳይ አስፍተን ሳይሆን አጥብበን ማየትና ማሳየት ይኖርብናል። መጽሃፍ ቅዱስ ሳይንሳዊ ቲዮሪዎችንና የሳይንስ መጻህፍቶችን ተክቶ መቆም የሚችል መጽሃፍ አስመስለው የሚያቀርቡ ተሰሚነት ያላቸው ሰባኪዎች ቁጥር ቀላል አይደለም። አዲስ ግኝቶችን ይጠቅሱና፣ ይህን ግን “መጽሃፍ ቅዱስ ከስንትና ስንት ሺህ ዓመታት በፊት ተናግሮታል” ይላሉ። ሳይንስን የሰይጣን ያክል ጠላትነት እንዳለው በሚያስመስል መልኩ ደግሞ፦ “ሳይንስ እንዲህ ይላል፣ መጽሃፍ ቅዱስ ግን እንዲህ ይላል፣ ጌታ ግን እንዲህ ይላል” የሚለውን መስማት የተለመደ ነው። እውነት እነዚህ ሰባኪዎች የሚሉት አይነት አንድነትና ግጭት በመጽሃፍ ቅዱስና ሳይንስ መካከል ኖሮ ሳይሆን፣ በአብዛኛው የመጽሃፍ ቅዱስን ዓላማ ወይም የሚጠቅሱትን ክፍል በተሳሳተ አረዳድ ከማየት ወይም ሳይንሱ የሚለውን ከማይለው ጋር በቅጡ ካለመለየት የሚመጣ ችግር ነው። ሰባኪው “ይህን ችግር ሳይንስ መፍትሔ አላገኘለትም” ወይም “ይህን በሽታ የሕክምና ባለሙያዎች መፍትሔ አላገኙለትም” ወይም “ለዚህ ጥያቄ ሳይንስ እስካሁን መልስ አላገኘለትም” ካለ ህዝቡ ለእግዚአብሔር ምስጋናውን፣ ለሰባኪው አድናቆቱን፣ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ “ጥላቻውን” በጭብጨባ ወይም በአሜን ወይም በእልልታ ይገልጻል። በቅርቡ በተካፈልኩት አንድ ፕሮግራም ላይ ሰፊ ተቀባይነት ያለው አገልጋይ የሐኪምን ማስረጃ ጭራሽ “የዲያብሎስ ማስረጃ” ብሎ ሲጠራ ስሰማ በጣም ግራ ገብቶኝ ነበር። እነዚህን አባባሎች ስሰማ፣ የምንገለገልባቸውን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶች (ማለትም ከምንለብሰው ልብስ ጀምሮ እስከምንነጋገርበት ድምጽ ማጉያ መሳሪያ፣ “ለአገልግሎት” እስከምንጠቀምበት ተሽከርካሪ) ቀምቶ፣ እስኪ መጽሃፍ ቅዱሳችሁን ብቻ አንብባችሁ ፍጠሩት ብሎ ማየት ነበር እላለሁ። ሰባኪው ምናለ “ለዚህ በሽታ ሳይንስ መድሃኒት አላገኘለትም” ብሎ ከሚያስጨበጭብና ለችግሮች ሁሉ መፍትሔ “የተቀቡ” ሰዎች ብቻ እንደሆኑ እያስመሰለ በሳይንስ እርዳታ የተጣራውን፣ የታሸገውንና የተጓጓዘውን ዘይት የሰዎች ግንባር ላይ ከሚያፈስ፣ “በእኛ መካከል ያላችሁ ልጆቻችን፣ ተማሪዎቻችን፣ ተመራማሪዎቻችን በእግዚአብሔር እርዳታ ለዚህ ደዌ መድሃኒት ፣ ለዚህ ጥያቄ መልስ፣ ለዚህ ችግር መፍትሔ ታገኛላችሁ” ቢል እያልኩ በውስጤ እመኛለሁ። እንዲህ ያለው ባህል፣ ለምክንያታዊነትና ምርምር ተገቢውን ቦታ እንዳንሰጥ አድርጓል። የሳይንስ ተጠቃሚዎችና ተባባሪዎች ሳንሆን ባላንጣዎች እንደሆንን እንዲሰማን አድርጓል፣ በሳይንስና ምርምር ውድቀት ክርስትናችን የሚያብብ አስመስሎታል። ለችግሮቻቻን መፍትሄ እግዚአብሄር በሰጠን አእምሮ ተጠቀሞ ሳይንሳዊ መፍትሔዎችን ማፈላለግ ከአለማዊነት ጎራ የሚያስመድብ አስመስሎታል። በዚህም ምክንያት ቀላል የማይባል የአማኝ ቁጥር የችግሩ ሁሉ መፍትሔ በሆነ ነብይ ወይም ቃል ወይም ጸሎት ወይም ቤተ ክርስቲያን ወይም ፕሮግራም እጅ ውስጥ እንዳለ እንዲያስብ ተደርጓል። ሰው በሽታ ወይም ስኬት ማጣት ወይም ድህነት ወይም ከሰው ጋር አለመስማማት ወይም በስራ አለማደግ ወይም በትምህርት መውደቅ ሲገጥመው የችግሩን ምንጭ ከመመርመርና ከጸሎት ጋር “ተፈጥሯዊ” መፍትሔ ከማፈላለግ ይልቅ ትንቢትንና አገልጋዮችን ፍለጋ ጊዜውንና ገንዘቡን ያባክናል። ልጆቻችን ፈሪሃ እግዚአሔር ያላቸው፣ ጌታን የሚወዱና የሚከተሉ ሐኪሞች፣ ሳይንቲስቶችና ተመራማሪዎች እንዲሆኑ ከማበረታታ ይልቅ፣ “የተአምር” ተስፈኛ የሆኑ ወይም እነሱ ራሳቸው ተአምር አድራጊ የሆኑ “የተቀቡ” አገልጋዮች ሆነው ማደግን እንዲመኙ እያደረግናቸው ያለ ይመስለኛል። ቤተ ክርስቲያን ከሙዚቀኞችና ከ”ተቀቡ” አገልጋዩች ያለፈ ለማህበረሰቡ የምታበርክታቸው ሌሎች ብዙ ባለ ሙያዎች እንዳሉ ለልጆቻቻን በግልጽ ማሳየት ይኖርብናል። የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶችን ተጠቃሚዎች ብቻ ሳንሆን በሳይንስና ምርምርም ማህበርተኛ መሆናችን ሊታወቅ ይገባዋል። ለችግር ሁሉ ቁልፉ “ተአምር” እንደሆነ የሚያስብን ምዕመን ማፍራት አሁን ለሚታየው ከየትም ፍጪው ትንቢቱን አምጪው ለሆነ ልምምድ አሳልፎ ሰጥቶናል። ያልጠበቅነው ወይም ስለነገሩ በቂ ግንዛቤ የሌለን ጉዳይ ሲገጥመን መጥፎ ከሆነ ከክፉ መናፍስት እንደመጣ ጥሩ ከሆነ በተአምር እንደሆነ አድርገን ማሰብ ሌሎችን እንደዛ እንዲያስቡ ማድረግ አሁን እየታየ ላለው “ፕሮቴስታንቱን ምን ነካው?” ለሚያስብለው ችግር ብቻ ሳይሆን ገና ለወደፊት እንግዳ ለሆኑ ብዙ ልምምዶች ይዳርገናል ብየ እፈራለሁ።

ከድጡ ወደ ማጡ

ችግሮች የኢትዮጵያውያን አማኞች ወይም የዚህ ዘመን አማኞች ብቻ እንዳልሆኑ ግልጽ ነው። በሐዋሪያቱ የተመሰረቱት የመጀመሪያዎቹ አብያተ ክርስቲያናት እንኳ ብዙ አይነት ችግሮች እንደነበሩባቸው ቅዱስ መጽሃፍ ምስክር ነው። እንደዚህ ያሉ ፈታኝ ጊዜዎችን እንደቀደሙት የእምነት አባቶች ራሳችንን ለመመርመርና ለማጥራት እድል የሚፈጥሩልን ጥሩ አጋጣሚዎች አድርገን መዋጀት አለብን እንጂ በመደናገጥና ተስፋ በመቁረጥ ከወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት መሸሽ የለብንም። አንዳንድ እንቅፋቶችን ሽሽት የትምህርትና የእንቅስቃሴ ማዕከሏን የክርስቶስን ወንጌል ካደረገች ቤተ ክርስቲያን ወጥተን ወንጌሉን ከሌላ ፍልስፍናና ባህል ጋር ወደ ቀየጡ “ጥንታዊያን” ግን እንግዳ ወንጌል ወደ ተሸከሙ የእምነት ተቋሞች መሄድ ከድጡ ወደ ማጡ ነው። አሁን በዚህ ዘመን ለብዙዎች ምሳሌ መሆን የሚችሉ፣ ከላይ ያነሳኋቸው ችግሮች ሰለባ ያልሆኑ በጣም ብዙ የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት፣ አገልጋዩችና ምዕመናን አሉን። እነዚህን በተለያየ ታሪክና ሁኔታ ላይ ያሉ ወንጌላዊያን አማኞችንና የእምነት ተቋሞችን በአንድ ጨፍልቆ የተመሳሳይ ችግሮች ሰለባ እንደሆኑ አድርጎ ማቅረብ ትክክል አይደለም፣ እኔም አላልኩም። አሁን በኢትዮጵያ እየሆነ ላለው ግሩም የወንጌል ስራ በበጎ ትጽዕኗቸው ለምሳሌነት መቅረብ የሚገባቸው ብዙ አብያተ ክርስቲያናትና አገልጋዮች መኖራቸውንም መዘንጋት የለብንም። ሀይላችንንና ሀሳባችንን ከእነርሱ ጋር አስተባብረን አረሙን በመንቀል የተተከለውን እውነተኛ የወንጌል ዘር ካፈራው በላይ እንዲያፈራ መስራት አለብን።

መቋጫ

ቁጥሩ ጥቂት ይሁን ብዙ፣ አይደለም በወንጌል የተዋጀን ቅዱስ የእግዚአብሔር ህዝብ፣ የማናውቀው መንገደኛ ሲታለልና ጥቅሙ ያላግባብ ሲወሰድበት ማየት ያሳዝናል፣ ያሳምማል፣ ያስቆጫል። እኔም ይህ ቁጭት ካደረባቸው ሰዎች አንዱ እንደመሆኔ ለመፍትሄ እንደሚሆን ተስፋ አድርጌ ያለኝን ጥቂት ግንዛቤ ለመግለጽ ይህን ጽሁፍ ጽፌአለሁ። ለመንጋው ሲሉ ሐሰተኞችን መመርመርና ማጋለጥ ከመሪዎች የሚጠበቅና ቸል መባል የሌለበት ሀላፊነት ነው። ምንም የመሪነት ድርሻ ባይኖረኝም፣ ይህን ሀላፊነት የሚወጡ መሪዎች ደጋፊ እንጂ ተቃዋሚ አይደለሁም። ሌሎችን ለማጋለጥ የምንጠቀምበት መስፈሪያ ግን በመጀመሪያ መርማሪዎች ነን በምንል በእኛ ይሁን በእኛ ዙሪያ ባሉ አገልጋዩችና ልምምዶች ላይ ጥቅም ላይ ሲውል መታየት አለበት። የጸዳ ስፍራ ሲቆሽሽ ያስታውቃል። እነዚህን ተጠያቂነትን የሚያዳክሙ፣ ጥበብንና ምርምርን የሚያጣጥሉ፣ ይሉኝተኝነትንና መስሎ ማደርን የሚያስፋፉ ልማዶችን ከነባሮቹ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ማስወገድ ቀጥሎ ለሚደረገው ሐሰተኞችን የማጋለጥ ስራ ወሳኝ ነው። ህዝቡም እንደገና ስህተት የሆነውንና ያልሆነውን መንፈስ ደግሞ እንለይልሃለን በሚሉ ሌሎች አገልጋዮች ወዲያና ወዲህ ከመላጋት ይጠበቃል። መለኪያችን አማኙን ግራ በማያጋባ መልኩ አጥቢያና አገልጋይ ሳይለይ ወጥነት ባለው መልኩ ስራ ላይ ሊውል ይገባል። እንደዚያ ያደረገን ቀን አሁን ያለው አሳሳቢ ሁኔታ ተቀይሮ ትምህርታችንንና ልማዳችንን እንደ እግዚአብሔር ቃል ለማጥራት የሚጠቅም በጎ የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ እንደሚያልፍ ተስፋ አደርጋለሁ።

 

እግዚአብሔር ያክብራችሁ!

Leave a comment