መግቢያ 

በዚህ ዙሪያ የግሌን አስተያየት ብሰጥ ጥሩ ነው ብየ ያሰብኩት በሐዋርያ ብስራት ብዙአየን (ጃፒ) የተሰጡትን “ሰው ምንድን ነው” ተከታታይ ትምህርቶች በዩቲዩብ ካየሁ በኋላ ነው። ይህን ጽሁፍ ከማንበብ በፊት “ሰው ማን ነው?” ክፍል 1 ትምህርትን መመልከት ንባቡን ቀላልና ፍሬያማ ያደርገዋል።

“ሰው መንፈስ ነው፣ ነፍስ አለው በስጋ ውስጥ ይኖራል” የሚለውን ትምህርት ጌታን ከተቀበልኩ ጥቂት ዓመታት በኋላ ተምሬ እኔም በዙሪያየ ላሉ ጥቂት ሰዎች ለጥቂት ጊዜ በቅናት አስተምሬ ነበር። እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር በ1990ዎቹ መጀመሪያና አጋማሽ አካባቢ እየተመሰረቱና እየተስፋፉ የነበሩ አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናትንና እንቅስቃሴዎቻቸውን በቅርብ ይሁን በሩቁ ትከታተሉ የነበራችሁ ይህ ትምህርት ምን ያህል ሰፊ ሽፋን ተስጥቶት እንደነበር እንደምታስታውሱ ተስፋ አደርጋለሁ። ወቅቱን ካስታዎሳችሁ የማይልስ ሞንሮ (Myles Munroe) ከዚህ አስተምህሮ ጋር የሚስማሙ ስብከቶቹ በቪዲዩ በስፋት ይሰራጩ የነበረበት ጊዜ ነው። እኔም በዚህ ጊዜ ነበር ይህን ትምህርትና ከትምህርቱም ጋር ተያይዘው የሚመጡ አንዳንድ ልምምዶችን ለመቀበልና ለመለማመድ የበቃሁት። አሁን ያ ከሆነ 15 ዓመታት ቢያልፉም ከዚያ እንቅስቃሴና አስተምህሮ ያተረፍኳቸው በጎ አተያዮችና ልምምዶች እስካሁን አብረውኝ አሉ። በአንጻሩም መጽሃፍ ቅዱሳዊ ድጋፋቸው እምብዛም ስለሆነብኝ የጣልኳቸው አስተምህሮዎችና ልምምዶችም አሉ። ከነዚህ ትምህርቶች አንዱ “ሰው ነፍስ ያለው በስጋ ውስጥ የሚኖር መንፈስ ነው” የሚለው ነው። በዚህ አስተምህሮ ውስጥ ስላለፍኩ ይሆናል ትምህርቱን መቀበሌን ልተው እንጂ አስተምህሮው በራሱ የኑፋቄ ትምህርት ነው ለማለት ግን አልደፍርም። በእኔ መረዳት አንድ ትምህርት ኑፋቄ ለመባል ከክርስትና አንኳርና መሰረታዊ አስተምህሮዎች ያፈነገጠ ሊሆን ይገባዋል። ይህ ትምህርት ልዩ አስከትሎቶች እስከሌሉት ድረስ መሰረታዊ ከሆኑ መጽሃፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮዎች ያፈነገጠ ሆኖ አይታየኝም። ይህን ስል ግን መጽሃፍ ቅዱስን በጥንቃቄ ከትውፊት፣ ከወግና ከጊዜው ፍልስፍና በነጻ አእምሮ ለሚያነበው ሰው ፈጽሞ የማይዋጥ እንደሆነ መዘንጋቴ እንዳልሆነ ማሳስብ እፈልጋለሁ። ታዲያ መጽሃፍ ቅዱሳዊ ድጋፉ በጣም የሳሳ ከሆነ እንዴት የኑፋቄ ለማለት ከበድህ ብሎ የሚጠይቅ ሰው ይኖር ይሆናል? የመጀመሪያው ምክንያቴ ከላይ እንደጠከስኩት ትምህርቱ በራሱ መሰረታዊ ከሆኑ የክርስትና አስተምህሮዎች ያፈነገጠ ለመሆኑ በቂ ማስረጃ ስላላገኘሁ ሲሆን ሁለተኛው ምክንያቴ ደግሞ በኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት የታቀፉ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት መጽሃፍ ቅዱሳዊ ድጋፋቸው ወደ ዜሮ የተጠጉ አንዳንድ ልምምዶችና አስተምህሮዎች ቢኖሯቸውም ኑፋቄ ብለን ስለማንጠራቸው ነው። ለምሳሌ ያክል ከልምምዶች ገና ለእምነት ያልደረሱ ህጻናትን ማጥመቅን መጥቀስ ይቻላል። ከአስተምህሮ ደግሞ ቅዱሳን ከጌታ መምጣት ጥቂት ዓመታት ቀደም ብለው ይነጠቃሉ የሚለውን መጥቀስ ይቻላል። የዚህ አስተምህሮ መጽሃፍ ቅዱሳዊ መሰረት እጅግ በጣም ደካማ ቢሆንም በብዙ ሰባኪዎችና አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ሰፊ ተቀባይነት ያለው ነው። ይህን ትምህርት ኑፋቄ ለማለት በሚያስችል መልኩ ግን ከመሰረታዊ የክርስትና ትምህርት ያፈነገጠ ሆኖ አላገኘሁትም ስለዚህም ኑፈቄ ለማለት አልደፍርም በትምህርቱ ባይሳማሙም ኑፋቄ ግን አይደለም ከሚሉ ሰዎችም ጋር እስማማለሁ። ይህንን የመሰሉ ልምምዶችንና ትምህርቶችን ኑፋቄ አይደሉም ካልን በኋላ፣ “ሰው መንፈስ ነው” የሚለውን ትምህርት ኑፋቄ ማለት ግን ሁለት ዓይነት ሚዛን መጠቀም ይሆንብኛል። እኛም ራሳችን ደግሞ “መናፍቃን” እየተባልን ብዙ ጊዜያትን እንደማሳለፋችን፣ የማንስማማበትን አስትምህሮ ሁሉ ኑፋቄ ማለት ከእኛ የሚጠበቅ አይመስለኝም። ታዲያ ኑፋቄ ካልሆነማ ትምህርቱ ተቀባይነት ሊያገኝ ይገባል የሚል ሰው አይጠፋ ይሆናል። አንድን ትምህርት ላለመቀበል የምናስቀምጠው መመዘኛ ኑፋቄ መሆኑ ብቻ መሆን የለበትም። ብዙዎቻችን ለቅዱሳን መጻህፍት ታማኝ አይደለም ብለን እናት አባት ያቆዩንን ሃይማኖት ጥለን እንደመምጣታችን የምንቀበለውንና የምናስተምረውን ትምህርት ሆነ ልምምድ መጽሃፍ ቅድሳዊ መሰረቱን በጥንቃቄና በጥልቀት መመርመር ይኖርብናል። በራሳቸው ሲታዩ ለኑፋቄነት የማይበቁ ጥቃቅን ስህተቶች ሲደራረቡ ኑፋቄ ውስጥ ሊከቱ ይችላሉና። ታዲያ ይህን ጽሁፍ ለመጻፍ ምን አነሳሳህ ካላችሁኝ ቀድም ብየ እንዳልኩት ጥቃቅን ስህተቶች ሲደራረቡ ኑፋቄ ውስጥ ሊከቱ ይችላሉ የሚል እምነት ስላለኝ መሆኑ አንዱ ቢሆንም ዋናው ምክንያቴ ግን ከመጽሃፍ ቅዱስ አፈታት ዘዴያችን ጋር የተገናኘ ነው። በተለይም አብዛኞቻችን ለመጽሃፍ ቅዱስ ተገቢውን ትኩረት አልሰጠም ብለን ካሰብነው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት እንደመምጣታችን መጽሃፍ ቅዱስን በአግባቡና በጥንቃቄ መረዳት፣ መፍታትና ማስተማር ምን ያህል ለድርድር የማይቀርብ መሰረታዊ ነገር እንደሆነ የምንዘነጋው አይመስለኝም። መጽሃፍ ቅዱስን ጸሃፊውና ጸሃፊውን የነዳው መንፈስ ቅዱስ ሊያስተላልፉ የፈለጉትን ሃሳብ ለመረዳት በሚያስችል ከራስ አጀንዳ በነጻ አእምሮ፣ የራሳችንን ስሜትና የቀደሙንን ሰዎች ወግ ለማስጠበቅ ባልሆነ ልቦና ልናነበው ይገባናል። በዚህ ጽሁፍ ሐዋርያ ጃፒ “ሰው መንፈስ ነው” የሚለውን ትምህርት ለማስተማር የተከተለው አረዳድና አፈታት ለምን ትክክል እንዳልሆነና ያለውንም አደጋ ለማሳየት እሞክራለሁ። የጃፒ አገልግሎት ብዙ ሰዎችን እየጠቀመ እንደሆነ ተስፋ አደርጋለሁ መጥቀሙንም እንዲቀጥል ፍላጎቴ ነው። የዚህም ጽሁፍ ዓላማ የ “ሰው መንፈስ ነው” ትምህርትን ለመደገፍ የሚሰጡትን መጽሃፍ ቅዱሳዊ መረጃዎች ደካማነት በማሳየት ከዚህ አስተምህሮ ጋር ንክኪ ያላቸው ክርስቲያኖችና አገልግሎቶች ይህን ከመሰለ ደካም ልምምድ እርምት ወስደው ፍሬያማ እንዲሆኑ መርዳት ነው።

ልዩነቱ 

በኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት የሚታመንበት እኔም መጽሃፍ ቅዱሳዊ ነው ብየ የምስማማበት አስተምህሮ “ሰው መንፈስ፣ ነፍስና ስጋ ነው”1 የሚል ሲሆን ከዚህ የሚጻረር ነው የሚባለው በጃፒ፣ ከእርሱ በፊትና ከእርሱ ጋር በሌሎች ሰዎች እየቀረበ ያለው አስተምህሮ ደግሞ “ሰው መንፈስ ነው፤ ነፍስ አለው፤ በስጋ ውስጥ ይኖራል” የሚል ነው። ለመሆኑ “ሰው መንፈስ ነው፤ ነፍስ አለው፤ በስጋ ውስጥ ይኖራል” ማለት ምን ማለት ነው? ይህ አገላለጽ ባጭሩ ሰውን ሰው የሚያስብለው መንፈስ ብቻ ነው የሚለውን መልዕክት የያዘ ነው። በአይናችን የምናነየው ሰው ስጋ የለበሰ መሆኑን አይክድም ወይም ነፍስ የምትባል ተጨማሪ ነገር እንዳለችው አይክድም ነገር ግን አንድን ሰው “ሰው” ለማስባል መንፈሱ ብቻ በቂ ነው ባይ ነው። በዚህ ትምህርት ሰው የሚለውም ቃል የሚያመለክተው መንፈስን እንጂ የለበሰውን ስጋ ወይም እንደ ተጨማሪ ነገር የያዘውን ነፍሱን አይደለም ማለት ነው። ይህን ትምህርት የሚቀበሉ ወይም የሚያስተምሩ ነገር ግን አሁን በሰጠሁት አጭር የትምህርቱ ማብራሪያ የማይስማሙ ይኖራሉ። ለእነርሱ ይህ ትምህርት አንድን ሰው “ሰው” ለማለት የግድ መንፈስ፣ ነፍስና ስጋ ሊኖረው ይገባል ይሉ ይሆናል፣ “ሰው መንፈስ ነው፣ ነፍስ አለው በስጋ ውስጥ ይኖራል” የሚለውም አባባል ዋናው መንፈስ መሆኑን ለማመልከት እንዲሁም የአንድን ሰው እጣ ፈንታ ወሳኙ መንፈሱ ነው ለማለት ነው እንጂ ስጋና ነፍስ ሰው ለመሆን ያላቸውን አስፈላጊ ድርሻ ለመካድ አይደለም ይሉ ይሆናል። በእኔ አመለካከት እነዚህ ሰዎች ምናልባት ወይ ትምህርቱን በደንብ አልተረዱትም ወይንም ይህንን አቋማቸውን ለመግልጽ “ሰው መንፈስ ነው” ከሚለው ቃል ይልቅ አወዛጋቢ ያልሆነ በመጽሃፍ ቅዱስም እንደ “መንፈሳዊ ሰው”፣ “በመንፈስ የሚመላለሱ”፣ “በመንፈስ የሚመሩ”፣ “በውስጥ ሰውነታቸው የጠነከሩ” እና ሌሎች ብዙ በስፋት የዋሉ የተሻሉ አገላለጾች እንዳሉ ዘንግተዋል ማለት ነው። ይህን ትምህርት “የእግዚአብሔር ቃል የሚለኝን፣ ጌታ የሚለኝን፣ በመንፈስ የሆንኩትን እንጂ ስጋዊ ወይም አለማዊ ወይም ማህበረሰባዊ መለኪያ የሚለኝን አይደለሁም” ለማለት ብቻ የተቀበሉ ሰዎች ካሉም ይህን ለማለት “ሰው መንፈስ ነው” የሚለውን አገላለጽ መጠቀም አላስፈላጊ እንደሆነ ለማሳሰብ እወዳለሁ። ይልቅ ከላይ በመጽሃፍ ቅዱስ በስፋት እንደዋሉ የዘረዘርኳቸውን ዓይነት ቃላት በመጠቀም ከአላስፈላጊ ውዝግብ ራሳቸውንም ሌሎችንም እንዲያድኑ እመክራለሁ። ልዩነትም ክርክርም ጽንሰ ሃሳባዊ ሲሆን እንጂ ተመሳሳይ ጽንሰ ሐሳብን በአወዛጋቢ ቃላት እየገለጹ አጉል የ “ቃላትና የስሞች”2 ክርክር መፍጠር ሲሆን ደስ አይልም።

የትምህርቱ መሰረተ ሐሳቦች 

ለ“ሰው መንፈስ ነው” አስተምህሮ እንዲሁም ለአስተምህሮው ምላሽ ጥቅም ላይ የሚውሉ ብዙ ነገረ መለኮታዊ ወይም ፍልስፍናዊ ወይም ልምምዳዊ መከራከሪያዎች ሊቀርቡ ይችላሉ። በዚህ ጽሁፍ ግን በመግቢያው እንደገለጽኩት ትምህርቱን ለመደገፍ በተለይም በብስራት ብዙአየን (ጃፒ) የቀረቡትን መጽሃፍ ቅዱሳዊ የመከራከሪያ ነጥቦች ብቻ እንገመግማለን። በእኔ ግምት “ሰው መንፈስ ነው” ከሚለው ትምህርት ይልቅ አሳሳቢው ትምህርቱን ለመደገፍ የሚቀረቡትን ጥቅሶች ለመተርጎም የሚወሰደው አካሄድ ነው። ትምህርቱን ለመደገፍ የሚሰጡ ብዙ ጥቅሶች አሉ፣ በተለይ አንዴ ትምህርቱን ከተቀበላችሁት መጽሃፍ ቅዱስን  “ሰው መንፈስ ነው” በሚል አዲስ መነጸር ስለሆነ የምታነቡት፣ ሲሆን ከእያንዳንዱ ምዕራፍ አለዚያ ቢያንስ ቢያንስ ከእያንዳንዱ የብሉይና የአዲስ ኪዳን መጻህፍት “ሰው መንፈስ እንደሆነ” የሚያሳይ ጥቅስ አታጡም። ለዚያ ሁሉ ምላሽ መስጠት የዚህ ጽሁፍ ዓላማ አይደለም ትርፋማ አካሄድ ነው ብየም አላምንም። ይልቁን ከራሴ ልምድ እንዲሁም ትምህርቱን ባስፋፉ ሰዎች የሚቀርቡ ለትምህርቱ መሰረት ጣይ ናቸው ብየ ያሰብኳቸውን የመከራከሪያ ነጥቦች እዳስሳለሁ። ሙግቴም እንዴው ነፋስን እንደመጎሰም እንዳይሆንብኝ፣ ጃፒ “ሰው ማን ነው” በሚለው ክፍል አንድ ትምህርቱ የቀረቡትን ነጥቦችና ጥቅሶች መሰረት አደርጋለሁ። የጃፒ መከራከሪያ ነጥቦች ሲጨመቁ በእነዚህ ሶስት ዋና ዋና ኦሪት ዘፍጥረታዊ ጽንሰ ሐሳቦች ይጠቃለላሉ ብየ አስባለሁ (እነዚህ ነጥቦች የጃፒ እንጂ የእኔ አይደሉም)፦

  1. እግዚአብሔር ሰውን በመልኩ እንደምሳሌው ፈጥሮታል፣ የእግዚአብሔር መልክ ደግሞ “እግዚአብሔር መንፈስ ነው” ስለሚል በመልኩ የፈጠረው ሰው መንፈስ ነው።
  2. አንድ ነገር ተፈጠረ የሚባለው ከዚህ በፊት ካልነበረ ነው። አንድን አዲስ ነገር ቀድሞ ከነበረ ሌላ ነገር (ጥሬ ዕቃ) መስራት ደግሞ መስራት ወይም ማበጀት እንጂ መፍጠር አይባለም። የሰው ስጋ ቀድሞ ከነበረ የመሬት አፈር የተገኘ ስለሆነ ተፈጠረ አንለውም። በዘፍ 1፥27 ግን “ሰውን ፈጠረው” ስለሚልና “ፈጠረው” የሚለው ቃል ደግሞ ከአፈር የተበጀውን ስጋውን ሊያመለክት ስለማይችል በዚህ ክፍል የተፈጠረውና “ሰው” ተብሎ የተጠራው ያለምንምንም ጥሬ ዕቃ ካለመኖር ወደመኖር የመጣው መንፈስ ነው።
  3. እግዚአብሔር አዳምን ከዚህ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህ ብሎት ነበር፣ የሞተው ግን በስጋው ሳይሆን በመንፈስ ነው ስለዚህም “ትሞታለህ” በሚለው ቃል ውስጥ “አንተ” እያለ የጠራው ደግሞ መንፈሱን (የአዳምን) ስለሆነ አንተ ተብሎ የተጠራው ሰው መንፈስ ነው ማለት ነው።

የመጀመሪያው ነጥብ “የእግዚአብሔር መልክ” በሚለው ቃል፣ ሁለተኛው “ፈጠረ”ና “አበጀ” በሚሉት ሁለት ቃላት ላይ፣ እንዲሁም ሶስተኛ “አንተ”፣ “አንቺ”፣ “እርሱ”፣ “እርሷ”፣ “እናንተ”ና “እኔ” በሚሉት ተውላጠ ስሞች ወይም በጃፒ አገላለጽ “subject” አጠቃቀም ላይ የተመሰረቱ መከራከሪያዎች ናቸው። እስኪ አንድ በአንድ እንመርምራቸው።

1. የእግዚአብሔር መልክ 

እግዚአብሔር ሰውን በመልኩ ስለፈጠረው፣ ሰው ማነው የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ አስቀድሞ የእግዚአብሔር መልክ ምንድን ነው የሚለውን ጥያቄ መመለስ አስፈላጊ ነው። ለዚህም ጥያቄ ጃፒ የሚሰጠው መልስ “የእግዚአብሔር መልክ መንፈስ ነው” የሚል ነው። እግዚአብሔር መንፈስ እንደሆነ ፈጽሞ አጠራጣሪ አይደለም ይህንንም እውነት የሚያሳዩ በርካታ ጥቅሶች አሉ። ነገር ግን “እግዚአብሔር መንፈስ ነው” የሚለውን አገላለጽ “የእግዚአብሔር መልክ መንፈስ ነው” ወደ ሚል አባባል መቀየር ይቻላል ወይ የሚለው በጣም አጠያያቂ ነው። “እግዚአብሔር መንፈስ ነው” ወይም “ጌታ ግን መንፈስ ነው” የሚል ዓረፍተ ነገር እንዳለ ሁሉ እግዚአብሔር እንደዚህ ነው ወይም እንደዚያ ነው የሚሉ ሌሎች ብዙ ዓረፍተ ነገሮች በመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ አሉ። ለምሳሌ ያህል፦

“እግዚአብሔር ሕያው ነው”፣ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው”፣ “እግዚአብሔር ተዋጊ ነው”፣ “እግዚአብሔር ሃያል ነው”፣ “እግዚአብሔር  የእስራኤል አምላክ ነው”፣ “እግዚአብሔር ግን አንድ ነው”፣ “እግዚአብሔር ልዑል ግሩምም ነው”፣ “እግዚአብሔር ታጋሽና ምሕረቱ የበዛ፥ አበሳንና መተላለፍን ይቅር የሚል፥ ኃጢአተኞችንም ከቶ የማያነጻ፥ የአባቶችን ኃጢአት እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድ ድረስ በልጆች ላይ የሚያመጣ ነው”፣ “እግዚአብሔር አዋቂ ነው”፣ “እግዚአብሔር ዓለቴ አምባዬ መድኃኒቴ ነው”፣ “እግዚአብሔር ቸር ቅንም ነው”፣ “እግዚአብሔር ዓለቴ፥ አምባዬ፥ መድኃኒቴ፥ አምላኬ፥ በእርሱም የምተማመንበት ረዳቴ፥ መታመኛዬና የደኅንነቴ ቀንድ መጠጊያዬም ነው”፣  “እግዚአብሔር ለምድር ሁሉ ንጉሥ ነው”፣ “እግዚአብሔር የበቀል አምላክ ነው”፣ “እግዚአብሔር ታላቅ አምላክ ነውና፥ በአማልክትም ሁሉ ላይ ታላቅ ንጉሥ ነው”፣ “እግዚአብሔር የዘላለም አምባ ነው”፣ “እግዚአብሔር ፈራጃችን ነው”፣ “የክርስቶስ ራስ እግዚአብሔር ነው”፣ “እግዚአብሔር ብርሃን ነው”፣ “ጌታ ቅርብ ነው”፣ “ጌታ የታመነ ነው”፣ “ጌታ ስለዚህ ነገር ሁሉ የሚበቀል ነው”፣ “ጌታ እጅግ የሚምር የሚራራም ነው”።

እነዚህ ሁሉ እግዚአብሔር እንዲህ ነው ወይም ጌታ እንዲህ ነው በሚል ዓይነት ከተቀምጡ ዓረፍት ነገሮች በጣም ጥቂቶቹ ናቸው። የእግዚአብሔር ሌሎች መጠሪያዎችን ወይም “እርሱ” የሚለውን ተውላጠ ስም ከተጠቀምን፣ እንዲሁም በ“ነው” ፋንታ “ይሆናል”፣ “ነህ”፣ “የሆነ”፣ “የሆንህ”ና የመሰሰሉትን ከተጠቀምን ምናልባት የዓረፍተ ነገሮቹ ዝርዝር አንድ መለስተኛ መጽሃፍ ሊወጣው ይችላል። ይህን ሁሉ የዘረዘርኩበት ዓላማ “እግዚአብሔር መንፈስ ነው” ወይም “ጌታ ግን መንፈስ ነው” የሚለውን ቃል ወስደን የ“እግዚአብሔር መልክ መንፈስ ነው” የሚል ትርጉም መስጠት ምን ያህል የማያስኬድ አተረጓጎም እንደሆነ ለማሳየት ነው። በዚያ አካሄድ ከሆነ ነገ ደግሞ ሌላው ተነስቶ “እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፥ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው” ስለዚህ ሰው በእግዚአብሔር መልክ ተፈጠረ ስንል “ሰው የዘላለም አምላክ፥ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው” ሊል ነው ማለት ነው፣ ወይም አንዱ ተነስቶ “የእግዚአብሔር መልክ ተዋጊ ነው” ሊል ነው ማለት ነው። እግዚአብሔር እንዲህ ወይም እንዲያ ነው የሚሉት አገላለጾች አንዳንዶቹ ባህሪውን፣ ሌሎቹ ደግሞ መደቡን፣ ሌሎቹ ስልጣኑን፣ ሌሎቹ ዕውቀቱን ወይም ሃይሉን ወይም ስራውን የሚገልጹ ናቸው።

በእኔ መረዳት “እግዚአብሔር መንፈስ ነው” የሚለው ቃል የእግዚአብሔርን መደብ (class/kind) የሚገልጽ እንጂ በዘፍ 1፥27 ላይ ላለው “የእግዚአብሔር መልክ” ማብራሪያነት ሊውል የሚችል አይደለም። መደብ ስል እንደ እንስሳ፣ ሰው፣ ዕፅዋት፣ ቁስ፣ መንፈስ፣ ጠጣር፣ ፈሳሽ፣ መልአክ፣ ፍጡር፣ የሚታይ፣ የማይታይ፣ አይሁዳዊ፣ ግሪካዊ እና የመሳሰሉትን መግለጫዎችን ማለቴ ነው። “መንፈስ” የሚለው ቃል መደብ ገላጭ መሆኑን የሚያሳዩ ሁለት ምክንያቶችን ልስጥ። አንደኛው “እግዚአብሔር መንፈስ ነው” እና “ጌታ ግን መንፈስ ነው” የሚሉት ቃላቶች የሰፈሩባቸውን አውዶች (ዮሃ 4፥24 ፤ 2ቆሮ 3፥17) ስናይ ማስተላለፍ የተፈለገው መልእክት፦ እግዚአብሔር የሚዳሰስና የሚታይ አይደለም፣ በዚህ ወይም በዚያ ቦታ የተወሰነ አይደለም፣ በአጭሩ ቁስ አይደለም የሚለውን ነው። “መንፈስ ነው” ወይም “መንፈስ አይደለም” ስንል ዓላማው መደብን ማሳየት ነው፣ ያ ነገር ወይም አካል ቁስ አይደለም ለማለት ነው። ሁለተኛው “መንፈስ ነው” የሚለው አገላለጽ መደብን የሚያሳይ ነው እንድል የሚያደርገኝ፣ በመጽሃፍ ቅዱስ መላእክትና አጋንንቶች መናፍስት እንደሆኑ የሚገልጹ ጥቂት የማይባሉ ክፍሎች ስላሉ ነው። እግዚአብሔር ከዲያብሎስ ጋር ምንም ህብረት የለውም ግን ሁለቱም መንፈስ ናቸው። መንፈስነት መደባቸው እንጂ መልካቸው አይደለም፣ መንፈስነት መልካቸው ከሆነ ግን ክርስቶስ የእግዚአብሔር መልክ(ምሳሌ) እንደሆነ ሁሉ ዲያብሎስም የእግዚአብሔር መልክ(ምሳሌ) ነው ለማለት ልንገደድ። ያም ብቻ ሳይሆን ሰው በመላእክትም ወይም በአጋንንት ወይም በሌሎች መንፈስ በሆኑ ፍጥረቶች መልክ ነው የተፈጠረው ልንል ነው ማለት ነው። እንዲህ ያለው አተረጓጎም የእግዚአብሔርን መልክ ከመላዕክትና ዲያብሎስ መልክ ጋር የሚያደናብር ነው። “መንፈስ” የሚባለው መደብ ደግሞ ሰፊ ስለሆነ፣ ማለትም በውስጡ ቢያንስ እግዚአብሔር፣ መላዕክትና ርኩስ መናፍስት ስላሉ፣ ለመደብ መግለጫ የዋለን ቃል ወስደን የእግዚአብሔርን መልክ ለመተርጎም ከመጠቀማችን በፊት ከአነቃቂ መፈክርነት ያለፈ ጠንካራ ምክንያት ሊኖረን ይኖርብናል።

የእግዚአብሔር መልክ ማለት መንፈስ መሆን ማለት እንዳልሆነ ካየን እስኪ አሁን ደግሞ ስለ እግዚአብሔር መልክ መጽሃፍ ቅዱስ ራሱ ምን ይላል የሚለውን እንመልከት። “የእግዚአብሔር መልክ” ሲባል ባጭሩ ውስንነት ባለው መልኩ እግዚአብሔር የሆነውን መሆን ማለት እንደሆነ ለሁሉም ግልጽ ይመስለኛል። ይሁን እንጂ እግዚአብሔር የሆነውን ሁሉ መሆን እንዳልሆነም ግልጽ ጉዳይ ይመስለኛል። ከላይ የዘረዘርኳቸውንና መሰል እግዚአብሔር እንደዚህ ነው የሚሉትን ጥቅሶች ከመጽሃፍ ቅዱስ አውጥተን “ታዲያ ሰውም እንደዚህ ነው?” ብለን መጠየቁ፣ እግዚአብሔር የሆነውን ሁሉ ሰው እንዳልሆነ ሊሆንም እንደማይችል በቀላሉ ሊያሳየን ይችላል። ከራሱ ከዘፍጥረቱ ታሪክ ሳንርቅ ምዕራፍ 3 ቁጥር 22 ላይ “እነሆ አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ” ማለቱ በምዕራፍ 1፥27 በእግዚአብሔር መልክ ተፈጥሮ የተጠናቀቀው አዳም ገና እንደ እግዚአብሔር መልካምንና ክፉን የሚያውቅ እንዳልነበረ ሲነግረን በእግዚአብሔር መልክ መሆን ማለት እግዚአብሔር የሆነውን ሁሉ መሆን እንዳልሆነ ባጭሩ የሚያስረዳ ክፍል ነው። ሰው በእግዚአብሔር መልክ ተፈጥሯል ማለት ምን ማለት ነው የሚለውን ጥያቄ ስንጠይቅ ዓላማችን ሰው እንደ እግዚአብሔር የሆነው በምን ረገድ ነው የሚለውን ማወቅ ነው። በእግዚአብሔር መልክ መፈጠር ማለት ምን ማለት እንደሆነ ሊረዱን የሚችሉ ሁለት ጥቅሶች አንድ ከብሉይ ኪዳን አንድ ከአዲስ ኪዳን እንመልከት።

የመጀመሪያው ዘፍ 1፥26፣27 ነው፣ ክፍሉ የ“እግዚአብሔር መልክ” የሚለውን ቃል በተጠቀመበት ሁለት ጊዜ ሁሉ አያይዞ የሚያመጣው በምድር፣ በባህርና በአየር ላይ ያሉ እንስሳትን መግዛት የሚለውን ሐሳብ ነው። ከዚህ ጥቅስ ክፍሉ የሚፈቅድልልን ያክል ብቻ ካነበብን በእግዚአብሔር መልክ መፈጠር ማለት ምን ማለት ነው ለሚለው ጥያቄ የምናገኘው መልስ፦ “እንደ እግዚአብሔር ገዢ ወይም ንጉስ መሆን፣ እግዚአብሔር በፍጠረቱ ላይ ያለውን የሚመስል ቦታ መያዝ” የሚል ይሆናል። አሁንም ክፍሉ የሚፈቅድልንን ያህል ስናነብ ይህ ገዥነት ወይም ንግስና ልክ የእግዚአብሔር ዓይነት ስፋትና እርከን ያለው ሳይሆን በምድር፣ በባህርና በአየር ላይ ባሉ እንስሳት ላይ ብቻ የተገደበ ነው። ስለዚህ በዘፍጥረት 1፥26ና27 መሰረት የ“እግዚአብሔር መልክ” ስልጣንን ወይም በፍጥረት ላይ ያለን ቦታ ወይም ሹመትን አመልካች ነው ማለት ነው። ይህም ጽንሰ ሃሳብ በ2፥15 እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ወስዶ ያበጃትም ይጠብቃትም ዘንድ በዔድን ገነት አኖረው” ተብሎ ከተጻፈው፤ በ2፥19፣20 እግዚአብሔር አምላክም የምድር አራዊትንና የሰማይ ወፎችን ሁሉ ከመሬት አደረገ፤ በምን ስም እንደሚጠራቸውም ያይ ዘንድ ወደ አዳም አመጣቸው፤ አዳምም ሕያው ነፍስ ላለው ሁሉ በስሙ እንደ ጠራው ስሙ ያው ሆነ። አዳምም ለእንስሳት ሁሉ፥ ለሰማይ ወፎችም ሁሉ፥ ለምድር አራዊትም ሁሉ ስም አወጣላቸው፤” ተብሎ ከተጻፈው፤ እንዲሁም በመዝ 8፥3-8 የጣቶችህን ሥራ ሰማዮችን ባየሁ ጊዜ፥ ጨረቃንና ከዋክብትን አንተ የሠራሃቸውን፥ ታስበው ዘንድ ሰው ምንድር ነው? ትጐበኘውም ዘንድ የሰው ልጅ ምንድር ነው? ከመላእክት እጅግ ጥቂት አሳነስኸው፤ በክብርና በምስጋና ዘውድ ከለልኸው። በእጆችህም ሥራ ሁሉ ላይ ሾምኸው፤ ሁሉን ከእግሮቹ በታች አስገዛህለት፥ በጎችንም ላሞችንም ሁሉ ደግሞም የምድረ በዳውን እንስሶች፥ የሰማይንም ወፎች የባሕርንም ዓሦች፥ በባሕር መንገድ የሚሄደውንም ሁሉ ተብሎ ከተጻፈው ጋር አብሮ የሚሄድ ጽንሰ ሐሳብ ነው።

ሁለተኛው ኤፌ 4:24 ነው፣ ክፍሉን የበለጠ ግልጽ ለማድረግ ከአዲሱ መደበኛ ትርጉም ልጥቀስ “እውነተኛ በሆነው ጽድቅ እንዲሁም ቅድስና እግዚአብሔርን እንዲመስል የተፈጠረውን አዲሱን ሰው እንድትለብሱ ነው።” ይህ ትርጉም “እግዚአብሔርን እንዲመስል” ብሎ ያስቀመጠው ሐረግ አዲስ ኪዳን በተጻፈበት ጥንታዊ የግሪክ ቋንቋ “በእግዚአብሔር መልክ የተፈጠረውን” ወይም “በእግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን” ወይም “እንደ እግዚአብሔር እንዲሆን የተፈጠረውን” የሚል ትርጉም ያለው ሐረግ ነው። በዚህ ክፍል መሰረት አዲሱ ሰው የእግዚአብሔርን መልክ የሚመስለው በጽድቅና ቅድስና እንደሆነ ያስረዳናል። የክፍሉንም አውድ በደንብ ስናየው ከቁጥር 25 ጀምሮ ከጽድቅና ቅድስና ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ጉዳዩች በመዘርዘር ይህን ያዙና አድርጉ፣ ያንን ጣሉና አስወግዱ እያለ በመምከር የእግዚአብሔር መልክ ከስነ ምግባር (ሞራል) ጋር ተያያዥነት ያለው እንደሆነ በግልጽ ያሳየናል። ይህም ጽንሰ ሃሳብ በሌሎች ክፍሎችም የተደገፈ ጽንሰ ሃሳብ እንደሆነ የሚያሳዩንን ሁለት ክፍሎች ልጥቀስ። በዚያው መጽሃፍ ከክፍሉ ብዙም ሳንርቅ የሚገኘው የኤፌ 5፥1 ክፍል አንዱ ነው። “እንግዲህ እንደተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን ምሰሉ” ይልና ልናፈራቸውና ልናሳያቸው ስለሚገቡን የጽድቅና የቅድስና ፍሬዎች ከቁጥር 2-14 በመዘርዘር እግዚአብሔርን የምንመስለው በጽድቅና ቅድስና እንደሆነ ያሳየናል። ሌላኛው ይህንኑ የእግዚአብሔርን መልክ ከስነ ምግባር አንጻር ማየት ተገቢ መሆኑን የሚያጠናክርልን ክፍል ቆላስይስ 3፥10 ነው እንዲህ ይላል “የፈጣሪውን መልክ እንዲመስል በዕውቀት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችሁታል። ይህ ክፍል ከላይ ካየነው የኤፌ 4፥24 ክፍል ጋር ጥብቅ ተዛማጅነት ያለው ክፍል ነው። ሁለቱም አዲሱን ሰው “መልበስ” ከሚል ቃል ጋር አብረው ያስቀምጡታል፣ ሁለቱም አዲሱ ሰው በእግዚአብሔር መልክ የተፈጠረ እንደሆነ ያሳያሉ፣ ከፍ ብለን ደግሞ ኤፌ 4:23ን ከጨመርነው ሁለቱም ክፍሎች ለዚህ የአዲሱ ሰው መልክ መገለጥ የአእምሮ መታደስ ያለውን አስፈላጊነት ያሳያሉ። ምንም እንኳን በኤፌ4፥24 ላይ “መልክ” የሚለውን ቃል በቃል ባናገኝም በጣም ተጓዳኝ ከሆነው በራሱ በጳውሎስ ከተጻፈው የቆላ3:10 ክፍል ጋር ስናየው ክፍሉ እያወራ ያለው ስለ እግዚአብሔር መልክ እንደሆነ ያለጥርጥር መገንዘብ ይቻላል። እንዲሁም ቆላ3፥10 እንደ ኤፌ4፡24 “ጽድቅና ቅድስና” የሚሉትን ቃላት ባይጠቀምም በጣም ተጓዳኝ ከሆነውና በራሱ በጳውሎስ ከተጻፈው የኤፌ4፥24 ክፍል ጋር በማዛመድ ክፍሉ የሚያወራው ስለጽድቅና ቅድስና ነው ብሎ መደምደም ይቻላል። ቀጥሎ ያለውም ክፍል ማለትም ቆላ 3:11-14 ይህንኑ ሃሳብ በግልጽ የሚያሳይ ነው። በእግዚአብሔር መልክ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱት እንዳለን “ምህረትን፣ ርህራሄን፣ ቸርነትን፣ ትህትናን፣ የዋህነትን፣ ትዕግስትን ልበሱ”፣ “ይቅር ተባባሉ”፣ “ፍቅርን ልበሱት” ይለናል። አዲሱን ሰው ከእነ ምህረትና ፍቅር ጋር በተለዋዋጭነት እየተጠቀመበት እንዳለ በግልጽ ማየት ይቻላል።

ከላይ ባያናቸው ክፍሎች መሰረት ሰው በእግዚአብሔር መልክ ተፈጥሯል ማለት እግዚአብሔር በፍጥረት ሁሉ ላይ ገዥ እንደሆነ ሁሉ ሰው ምድር ላይ ባሉ ፍጥረታት ላይ ገዥ ሆኖ ተፈጥሯል ማለት ነው። ወይም “እግዚአብሔር ንጉስ ነው” እንደሚል ሰውም ንጉስ ነው ማለት ነው። አዲሱ ሰው የእግዚአብሔርን መልክ እንዲመስል ተፈጥሯል ማለት ደግሞ እግዚአብሔር ጻድቅና ቅዱስ እንደሆነ ሁሉ አዲሱ ሰውም እውነተኛ ጽድቅና ቅድስና እንዲኖረው ተፈጥሯል ማለት ነው። ይህ ማለት እነዚህ ሁለት ሃሳቦች በውስጣቸው ብዙ ዝርዝዝ የላቸውም ለማለት እንዳልሆነ፣ እንዲሁም ከህይዎታችን ጋር የሚዛመዱበት ሁለት ቀጭን መስመሮች ብቻ ናቸው ያሉት ለማለት እንዳልሆነ ማስገንዘብ እወዳለሁ። ሰባኪዎችና አስተማሪዎች ሳይጠመዘዝና ከወሰን ሳያልፍ ስፋትና ጥልቀት ባለው መልኩ ከህይዎታችንንና ከሌሎች የመጽሃፍ ቅዱስ ክፍሎች ጋር እያዛመዱ ሊያስተምሩንና ሊሰብኩት የሚገባው ጉዳይ ነው። ከዚህ በተረፈ ግን በዘፍ 1፥27 “የእግዚአብሔር መልክ” የተባለውን “መንፈስ መሆን” ብለን እንድንተረጉም የሚያደርገን አንድም ጥቅስ አላገኘሁም። ጃፒም “እግዚአብሔር መንፈስ ነው” የሚለውን ወደ “የእግዚአብሔር መልክ መንፈስ ነው” ብሎ ለመተርጎም ያስቻለውን ምክንያት አልነገረንም።

2. መፍጠርና ማበጀት 

ይህንኑ የመከራከሪያ ነጥብ ጃፒ ብቻ ሳይሆን ስመ ጥር የሆኑ እንደ ማይልስ ሞንሮ ያሉ አስተማሪዎች እንዲሁም ሞርሞኖች ሲጠቀሙበት ስላየሁ ሰፋ ያለ ምላሽ ለመስጠት እሞክራለሁ።

ጃፒ በዚህ ነጥቡ ማለት የሚፈልገው ይህን ነው፦ ምዕራፍ 2 ከምዕራፍ 1 ቀጥሎ ስለመጣ የእግዚአብሔር ስራ የሚተርክ እንጂ በምዕራፍ 1 ስለተጠናቀቀው የሰው ፍጥረት የተሰጠ ክለሳ ወይም ዝርዝር ማብራሪያ አደለም። አንድ ነገር ተፈጠረ የሚባለው ከዚህ በፊት ካልነበረ ነው፣ ከነበረ ነገር የተሰራ ከሆነ ግን ተፈጠረ ሳይሆን ተበጀ ነው የሚባለው ዘፍ 1 እና 2 የሚያወሩት ስለአንድ ጉዳይ ስላልሆነና የመፍጠርና የማበጀት ትርጉም የተለያየ ስለሆነ ዘፍጥረት 1፥27 እና 2፥7 ላይ ያሉት ክፍሎች አንድን ክንውን በተለያያየ አገላለጽ እንደሚያቀርቡ ተደርገው ሊተረጎሙ አይገባም። ዘፍ 1፥27 “ፈጠረው” ስለሚል ክፍሉ የሚያወራው ያለ ምንም ጥሬ ዕቃ መንፈስ የሆነ ሰው ስለመፈጠሩ ነው። ዘፍ 2፥7 ደግሞ “አበጀው” ስለሚል ክፍሉ የሚያወራው ቀድሞ ከነበረ ነገር ማለትም ከምድር አፈር የሰው ስጋ ስለመበጀቱ ነው ስጋው ከተበጀ በኋላ ቀድሞ በ1፥27 የተፈጠረው ሰው (መንፈስ) ወደዛ ስጋ በእግዚአብሔር እስትንፋስ አማካኝነት ገባ ሰውም ነፍስ ያለው ሆነ። ስለዚህ በጃፒ አገላለጽ፦ መንፈስ የሆነ ሰው በዘፍ 1፥27 ላይ ተፈጠረ፣ ከዚያ በዘፍ 2፥7 ላይ ስጋ ለበሰ በዚያም ቅጽበት ነፍስ ያለው ሆነ።

ይህን የመከራከሪያ ነጥብ ሳስብ ከዛሬ 15 ዓመት በፊት የነበረኝ ገጠመኝ ትዝ አለኝ። በጊዜው ለቅርብ ጓደኞቼ ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ የምመሰክር የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ነበርኩ። አንድ ጓደኛየንም እየጨከጨኩ ስላስቸገርኩት ለምን አንድ ቀን አብረን ወደ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አንሄድምና እኔን ከሚያስተምረኝ ሰው ጋር አገናኝቸህ እኔ ባለሁበት አትነጋገሩም አለኝ። እኔም ተስማምቼ በቀጠሯችን መሰረት ተያይዘን ወደ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አመራን። የሚያስተምረው ልጅ በእድሜው ከእኛ ትንሽ ከፍ የሚል እሱም የኛው ትምህርት ቤት ተማሪ የነበረ ግን በቤተ ክርስቲያኒቱ የዲያቆንነት ማዕረግ ያለው ልጅ ነበረ። መጽሃፍ ቅዱስን በቃሉ የማስታዎስ ብቃቱ በጣም የሚያስገርም ነበር። እንደሌሎቹ ተቀምጠህ መማር፣ ጥያቄም ካለህ መጠየቅ ትችላለህ እንጂ ካንተ ጋር ቁጭ ብየ አልከራከርም ስላለኝ፣ ለመማርና ለመጠየቅ እንደሌሎቹ ተቀመጥኩ። እሱም ካለፈው ሳምንት የቀጠለው ዛሬ የሚያስተምረው ክፍል “አንቺ ሴት፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?” የሚለው እንደሆነ ከ ዮሃ 2፥4 ጠቀሶ ማስተማሩን ቀጠለ። “ኢየሱስ ይህን ሲል ምን ማለቱ ነው?” ብሎ ጠየቀና “ይህን ለመመለስ መጀመሪያ ‘አንቺ ሴት’ ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ እንመልከት” አለ። ለዚህም ሁለት ጥቅሶችን ከዘፍ 2፥23 እና ዘፍ 4፥25 በመጥቀስ “ክርስቶስ ‘አንቺ ሴት’ ሲል ‘አንቺ አጥንት ከአጥንቴ፣ ስጋ ከስጋየ’ እንዲሁም ‘አንቺ ምትኬ’ ማለቱ ነው” አለን። ከትምህርቱም በኋላ የጥያቄ ጊዜ ሲደርስ እጄን አውጥቼ ያሉኝን ጥያቄዎች አቀረብኩ። “አንቺ ሴት” ለሚለው የሰጠኸው ትርጉም ትክክል አይደልም” አልኩ ቀጥየም “በተለይ ‘አንቺ ምትኬ’ ለማለት ነው ያልከው በእንግሊዚኛው አይስኬድህም” አልኩት። ሳብራራም “የአዳም ልጅ በእንግሊዝኛም ስሙ ‘ሴት’ ነው፣ ነገር ግን ‘አንቺ ሴት’ በሚለው ክፍል ላይ ግን እንግሊዝኛው ‘woman’ ነው የሚለው አልኩት። እርሱም በአማርኛው ትርጉም ላይ እንግሊዘኛን ፈራጅ አድርጌ ማቅረቤ እያሳቀው አሁን በጥራት የማላስተውሰውን ከቋንቋ ጋር የተገናኘ መልስ ሰጠና መልሼ እጄን ሳወጣ ከእኔ ጋር በመከራከር የተማሪዎቹን ጊዜ እንደማያጠፋ ነግሮኝ ወደ ቀጣይ ትምህርቱ ሄደ። ከዚያ ገጠመኜ በኋላ ሁልጊዜም የምከተለው አንድ ምክር አለኝ፦ በአጠቃላይ ጽንሰ ሃሳቡ ላይ ሳይሆን መጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ ባለ አንድ ቃል ላይ የተንጠለጠለን አስተምህሮ ከማስተማርህ በፊት ቃሉ በሌሎች ቋንቋዎች ምን ይላል፣ በተለይም ደግሞ ቃሉ ከብሉይ ኪዳን ከሆነ በዕብራይስጡ3፣ ከአዲስ ኪዳን ከሆነ በግሪኩ ምን ይላል የሚለውን አስቀድመህ ጠይቅ የሚል ምክር ነው። ወንድማችን ጃፒ ባቀረበው ሁለተኛው የመከራከሪያ ነጥብ ይህ ምክር ስለተጣሰ ነው ገጠመኜ ትዝ ያለኝ። ቋንቋው ሲለወጥ አብሮ የሚለወጥ ስነ አፈታት ካላችሁ እየተከተላችሁት ያለው አተረጓጎም ችግር እንዳለበት እርገጠኛ መሆን ትችላላችሁ፣ እግዚአብሔር ያንን አፈታት መግለጥ የፈለገው የ1954ቱን የአማርኛ ትርጉም ለሚያነቡ አማኞች ብቻ ነው ካላላችሁ።

ከቀላሉ ልጀምርና “ሰውም ህያው ነፍስ ያለው ሆነ” የሚለውን የአማርኛ ትርጉም ይዞ “ሰው ነፍስ አለው እንጂ ነፍስ አይደለም” የሚለው ትምህርት፣ ለዲያቆኑ እንዳልኩት እንግሊዝኛው ላይ ሲሄድ፣ እንግሊዝኛን ማን ፈራጅ አደረገው ካላችሁኝ ደግሞ፣ ዕብራስይስጡ ላይ ሲሄድ ወዳቂ ነው። ዕብራይስጡም እንግሊዝኛውም እንዲሁም ሌሎች ብዙ ቋንቋዎችና ራሱ አዲሱ የአማርኛ መደበኛ ትርጉም “ሰውም ህያው ነፍስ ሆነ” ነው የሚሉት። ከመውደቁ በፊት ስለነበረው የሰው ምንነት በአጭሩ የሚዳሰሰው ጳውሎስም በቆሮንቶስ መልዕክቱ ይህንኑ የዘፍጥረት ክፍል በመጥቀስ ይህንኑ ሃሳብ ያንጸባርቃል፦

እንዲሁ ደግሞ፦ ፊተኛው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ ተብሎ ተጽፎአል፤ ኋለኛው አዳም ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ። ነገር ግን አስቀድሞ ፍጥረታዊው ቀጥሎም መንፈሳዊው ነው እንጂ መንፈሳዊው መጀመሪያ አይደለም። የፊተኛው ሰው ከመሬት መሬታዊ ነው፤ ሁለተኛው ሰው ከሰማይ ነው። መሬታዊው እንደ ሆነ መሬታውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው፥ ሰማያዊው እንደ ሆነ ሰማያውያን የሆኑት ደግሞ እንዲሁ ናቸው። 1ቆሮ 15፥45-48

ይህ ክፍል የሚያወራው በሃጥያት ስለወደቀው ሰው እንዳልሆነ ልብ እንበል። ትዕዛዝ በመተላለፉ ምክንያት የሃጥያትን ዘር ስላስተላለፈው አዳም ሳይሆን እዚህ ላይ የሚያወራው ከአፈር የተበጀ ምድራዊ አካሉን ስላስተላለፈው ከውድቀት በፊት ስለነበረው አዳም ነው። በዚህ ክፍል ጳውሎስ የሚጠቅሰው ጥቅስ በዘፍ2፥7 ላይ ያለ አዳም ከመውደቁ በፊት ስለነበረው ማንነት የሚናገር ከፍል ነው። አስቀድሜ ያልኳችሁን “ነፍስ ያለው ሆነ” የሚለው አባባል የ1954ቱ የአማርኛ ትርጉም አገላለጽ ብቻ እንደሆነ በሚያጠናክር መልኩ የ1954ቱ ትርጉም ራሱ ጳውሎስ የጠቀሰውን የዘፍጥረት ክፍል “አዳም ህያው ነፍስ ሆነ ተብሎ ተጽፏል4 ብሎ እንዳስቀመጠውም ተመልከቱ። ይህን ክፍል በጥንቃቄ ስናየው አዳም አይደለም መንፈስ ሊሆን መንፈሳዊ ሰው እንኳን እንዳልነበረ የሚያስረዱ የሚመስሉ ንጽጽሮችን ተጠቅሟል። ንጽጽሮችም፦ ፊተኛው አዳም ህያው ነፍስ፣ ኋለኛው መንፈስ፤ ፊተኛው ከመሬት መሬታዊ፣ ኋለኛው ከሰማይ ሰማያዊ፤ አስቀድሞ ፍጥረታዊ፣ ቀጥሎም መንፈሳዊ።

“ሰው ነፍስ ያለው ሆነ” ከሚለው በተጨማሪ የ1954ቱ የአማርኛ ትርጉም ላይ ብቻ የተንጠለጠለ ሌላ ነገር እስኪ ጨምር ካላችሁኝ፣ “ስጋ ለባሽ”5 የሚለው የመጽሃፍ ቅዱስ አባባልን ብጠቅስ ደስ ይለኛል። ጃፒ ይህን አባባል “ሰው ስጋ ለባሽ እንጂ ስጋ አይደለም” ለማለት ተጥቅሞበታል። ይሁን እንጂ “ስጋ ለባሽ” ይሁን “ስጋ የለበሰ” ተብለው በአማርኛው ትርጉም የተቀመጡት ክፍሎች በሙሉ መጽሃፍ ቅዱስ በተጻፈባቸው ኦሪጂናል ቋንቋዎችም ይሁን በአብዛኛው ጥቅም ላይ በሚውሉት የእንግሊዝኛ ትርጉሞች “ስጋ” ተብለው ነው የተቀመጡት። ይህን የምለው ሰው ስጋ ነው ወይም ሰው ስጋ ብቻ ነው ለማለት ሳይሆን ወይም ስጋን እንደመኖሪያና ልብስ የሚያሳዩ ሌሎች ክፍሎች የሉም ለማለት ሳይሆን፣ ከሃሳብ ይልቅ አንዲት ቃል ወይም አባባል ላይ የተንጠለጠለ አስተምህሮ መከተል ያለውን አደጋ ለማሳየት ነው። እኛም እንደዚህ አንዲት ቃልና አባባል ላይ የምንጠለጠል ከሆነ እነዚህን ሰውን “ስጋ” በሚል ስያሜ የሚጠሩ ክፍሎች በመጥቀስ “ሰው ስጋ ብቻ ነው፣ ነፍስ ወይም መንፈስ የምትባል የማትታይ ክፍል የለችውም” እያሉ የሚያስተምሩ ብዙ አስተማሪዎችን መቃወም ምን ያህል ከባድ እንደሚሆንብን እናስብ።

ወደ ጃፒ መከራከሪያ እንመለስና በመፍጠርና በማበጀት የትርጉም ልዩነት ተነስቶ የሰጠውን ማብራሪያ እንገምግም። “አንድ ነገር ተፈጠረ የሚባለው ከዚህ በፊት ካለነበረ ነው” ብሏል። ይህ ትርጓሜው ብዙም አከራካሪ አይደለም፣ በዚህ ትርጓሜው መሰረት ከሆነ ደግሞ “ሰው ከምድር አፈር ተፈጠረ” ማለት የሚያስኬድ አባባል ነው። ምክንያቱም ከዚህ በፊት የነበረው አፈር እንጂ ሰው (የሰው ስጋ) ስላሆነ። እሱ ግን “ከዚህ በፊት ከነበረ ነገር የተሰራ ከሆነ ተበጀ ነው እንጂ ተፈጠረ አይባልም” ባይ ነው። ይህን አባባሉን ስናይ ለማለት የፈለገው አንድ ነገር ተፈጠረ የሚባለው ከዚህ በፊት ያልነበረ (አዲስ) ነገር ከመሆኑ በተጨማሪ ያለምንም ጥሬ ዕቃ የተገኘ ከሆነ ብቻ ነው ለማለት እንደሆነ እንረዳለን። ይህን ትርጉም ከየት አገኘው ብለን እንድንጠይቅ የሚያደርግ አተረጓጎም ነው። የትኛውም መዝገበ ቃላት ይሁን ማህበረሰብ “መፍጠር” የሚለውን ቃል በዛ ጽንሰ ሃሳብ አይተረጉምም፣ አይጠቀምም። አንድን ነገር ካለምንም ጥሬ ዕቃ፣ ከባዶ ነገር ማስገኘት ተዓምር ይባል ይሆናል ወይም እንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች “creation ex nihilo” የሚሉትን ቃል ይወክላል እንጂ ፈጠራ ብቻ ሊሆን አይችልም። እንግሊዝኛው “ex nihilo” የሚል ቃል “creation” ላይ ማስከተሉ በራሱ “create” የሚለው ቃል ከባዶ ነገር የሆነን ነገር ማስገኘት ተብሎ ሊተረጎም እንደማይችል ማሳያ ነው።

ይህን የመዝገበ ቃላትና የቋንቋን አጠቃቀም ወደ ጎን ትተን ራሱ መጽሃፍ ቅዱስ እነዚህን ቃላት እንዴት ይጠቀማል የሚለውን እንመልከት። መጽሃፍ ቅዱስ ሲሰጠን አብሮ የራሱ ሙዳየ ቃል ወይም መዝገበ ቃላት ስላተሰጠን ጥቅም ላይ የዋሉትን ቃላት ትርጉም ለማወቅ የተሻለው አማራጭ በሌሎች የመጽሃፍ ቅዱስ ክፍሎች እንዴት ነው ቃሉ ጥቅም ላይ የዋለው? አውዶቹስ ምን ዓይነት ትርጉም ይሰጣሉ? የሚለውን ማየት ነው። ለመጀመር ያህል እስኪ የአማርኛውን ትርጉም እንደ-የመጽሃፍ-ቅዱስ-ኦሪጂናል-ቋንቋ-የመጠቀምና ሌሎች ቋንቋዎችን ያለማመሳከር ችግር ውጤት ነው ያልኩትን ስህተት ላሳይ። የ1954ቱ የአማርኛ ትርጉም ዘፍ 1፥26፣27ን “እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ። እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።” ብሎ ተርጉሞታል። ኦሪጂናሉ ቋንቋ ይሁን ሌሎች ሰፊ ተቀባይነት ያላቸው የእንግሊዝኛ ትርጉሞች ግን ከዚህ በጥቂቱ ይለያሉ። የአማርኛው አዲሱ መደበኛ ትርጉምም ይህንኑ አተረጓጎም ከኦሪጂናል ቋንቋው በሚስማማ መልኩ እንዲህ ብሎ አስቀምጦታል “እግዚአብሔርሰውን በመልካችን፣ በአምሳላችን እንስራ በባህር አሶች፣ በሰማይ ውፎች፣ በክብቶች፣ በምድር ሁሉ ላይ፣ እንዲሁ በምድር በሚሳቡ ፍጡራን ሁሉ ላይ ስልጣን ይኑራቸውአለ። ስለዚህ እግዚአብሔር ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።” የ1954ቱ ትርጉም “እንፍጠር” አለ ከዛ “ፈጠረ” ሲለን ዕብራስይጡ ግን “እንስራ” አለ ካዛ “ፈጠረ” ይለናል። ይህ ጃፒ “ፈጠረ” ለሚለው ቃል አዲስ ትርጉም ባይሰጥ ኖሮ ተራ ሊባል የሚችል የትርጉም ልዩነት ሆኖ እናልፈው ነበር። ይህ የዕብራስይጡ አጠቃቀም የሚያሳየን “መፍጠር”ና “መስራት” በተለዋዋጭነት ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ እንደአውዳቸው ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ትርጉም ሊሰጣቸው የሚችሉ ቃላት እንደሆኑ ነው። መቼም “አንድ ነገር ‘ተሰራ’ የሚባለው ከባዶ ነገር ከተገኘ ብቻ ነው” የሚል መከራከሪያ እንደማይቅርብ ተስፋ አደርጋለሁ። በዘፍጥረት ምዕራፍ 1 ና 2 ትረካ ውስጥ የእግዚአብሔርን የመፍጠር ስራ በሶስት የዕብራይስጥ ቃላት ሰፍሮ እናየዋለን። እነዚህን የእብራይስጥ ቃላት አማርኛው “መፍጠር”፣ “መስራት”፣ “ማበጀት” በሚሉ ለኦሪጅናሉ ቋንቋ ታማኝ በሆኑ 3 ቃላት ሲተረጉማቸው እንግሊዝኛው ደግሞ “create” ፣ “make” እና “form” በሚሉ ቃላት ያስቀምጣቸዋል። እነዚህ ሶስት ቃላት ጃፒ የሚለውን አይነት ትርጉም ይዘው ጥቅም ላይ እንዳልዋሉ ለማሳየት፣ መጀመሪያ  “መፍጠር” የሚለው ቃል መስራት ከሚለው ቃል ጋር በተለዋዋጭነት መዋሉንና የጥሬ ዕቃ መኖር “መፍጠር” የሚለውን ቃል ከመጠቀም እንደማያግድ አሳያለሁ፣ ከዚያም “ማበጀት” የሚለው ቃል “መፍጠር”ና “መስራት” ከሚሉት ቃላት ጋር በተለዋዋጭነት መዋሉን አሳያለሁ፣ በመጨረሻም የጃፒን የዘፍጥረት 1 እና 2ን አተረጓጎም መከተል የሚያመጣውን የአፈታት ቀውስ አሳያለሁ።

መፍጠርና መስራትእግዚአብሔርም ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ [በመስራቱ] ተጸጸተ፥ በልቡም አዘነ። እግዚአብሔርም፦ የፈጠርሁትን ሰው ከምድር ላይ አጠፋለሁ፥ ከሰው እስከ እንስሳ እስከ ተንቀሳቃሽም እስከ ሰማይ ወፍም ድረስ ስለ ፈጠርኋቸው [ሰራኋቸው] ተጸጽቼአለሁና አለ።” ዘፍ 6፥6፣7። አማርኛው “መፍጠር” እያለ ቢያስቀምጣቸውም ትክክለኛውን የዕብራይስጥ ቃል የሚወክሉትን ቃላት በካሬ “[]” ቅንፍ አስቀምጫለሁ። ከዚህ ጥቅስ እንደምናየው መስራትና መፍጠርን አንድ ትርጉም እንዳላቸው ቃላት እያፈራረቀ (interchangeably) ይጠቀምባቸዋል። በዚህ በዘፍ 6፥6 ላይ “እግዚአብሔርም ሰውን በምድር ላይ በመስራቱ” የሚለውን ቃል በቃል በዘዳ4:32 “እግዚአብሔር ሰውን በምድር ላይ ከፈጠረው” በማለት ጸሃፊው “መስራት” የሚለውን ቃል “መፍጠር” በሚል ቃል በመተካት ብቻ አንዳቸው በሌላኛቸው ምትክ ያለምንም ችግር ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ ቃላት እንደሆኑ ያሳየናል። “መስራት”ና “መፍጠር” በተለዋዋጭነት ጥቅም ላይ ሊውሉ እንደሚችሉ የሚያሳዩ ሌሎች ብዙ ጥቅሶች ቢኖሩም ማስተላለፍ ለፈለግሁት ሃስብ የጠቀስኳቸው ሁለት ጥቅሶች በቂዎች ናቸው ብየ አምናለሁ። “መስራት” የሚለው ቃል ደግሞ ከባዶ ነገር አዲስን ነገር ማውጣት እንዳልሆነ የሚያከራክር አይመስለኝም። አይ ያከራክራል ካልን በክፍሉ ላይ “ከሰው እስከ እንስሳ እስከ ተንቀሳቃሽም እስከ ሰማይ ወፍም ድረስ ስለ [ሰራኋቸው] ተጸጽቼአለሁና” ማለቱን ልብ እንበል። እንስሶችን “ሰራሁ” እያለ ነው፤ ታዲያ የሰራቸው እንዴት ነው? ጥሬ ዕቃ ሳይጠቀም ከባዶ ነገር ነው የሰራቸው? ለሚለው መልስ የሚሰጠን ደግሞ ዘፍ 1:24 ነው፦ “እግዚአብሔርም አለ፦ ምድር ሕያዋን ፍጥረታትን እንደ ወገኑ፥ እንስሳትንና ተንቀሳቃሾችን የምድር አራዊትንም እንደ ወገኑ፥ ታውጣ፤ እንዲሁም ሆነ።” በማለት እንስሳት የተፈጠሩት(የተሰሩት) ከባዶ ነገር ሳይሆን ከመሬት እንደሆነ በግልጽ ያሳያል። እንዲሁም በዘፍ 2፥19 “እግዚአብሔር አምላክም የምድር አራዊትንና የሰማይ ወፎችን ሁሉ ከመሬት አደረገ” በማለት እንስሳት እንደሰው ጥሬ ዕቃቸው መሬት እንደሆነች ይነግረናል። “መስራት” ከባዶ ነገር መገኘትን እንደማያመለክት የሚያረጋግጥ አንድ ጥቅስ ልጨምርና ወደ ሚቀጥለው እንሄዳለን፦ “እግዚአብሔር አምላክም ከአዳም የወሰዳትን አጥንት ሴት አድርጎ ሠራት” ዘፍ 2፥22። እግዚአብሔር ሴትን የሰራት የአዳም አጥንትን (የነበረ ነገርን) በጥሬ ዕቃነት ተጠቅሞ ስለሆነ “መስራት” የሚለው ቃል “መፍጠር” ለሚለው ቃል ተለዋጭ ሆኖ በመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ ቢውልም ከባዶ ነገር መገኘትን እንደማያመለክት አይተናል። “መስራት” እንዲህ ሲሆን ትርጉሙ “መፍጠር” ለሚለው ቃል በተለዋጭነት መዋሉ ”መፍጠር” የሚለውም ቃል ተጠቃሚው ማህበረሰብና መዝገበ ቃላቱ ኣንደሚስማሙት የግድ ከባዶ ነገር፣ ያለጥሬ ዕቃ ካልመጣ የሚያስብል ትርጉም እንደሌለው የሚያሳይ ነው።

ከዘፍጥረት ወጣ ብልን “መፍጠር” የሚለው ቃል እንዴት ባለ አውድ ውስጥ እንደዋለ ደግሞ ስናይ፦ ሕዝ 21፥19 አንተም የሰው ልጅ ሆይ፥ የባቢሎን ንጉሥ ሰይፍ ይመጣ ዘንድ ሁለት መንገዶችን አድርግ [ፍጠር] ሁለቱም ከአንዲት ምድር ይውጡ፤ ምልክትም አድርግ [ፍጠር] በከተማይቱ መንገድ ራስ ላይ አድርገው።” መቼም የሰው ልጅ መንገድና ምልክትን ከባዶ ነገር እንደማይፈጥር ሁሉም። በዚህ ክፍል ግን እግዚአብሔር ለሰው ልጅ መንገድና ምልክትን እንዲፈጥር ያዘዋል። አማርኛው አድርግ ብሎ የተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል በዘፍ 1፥27 ላይ የዋለውን “መፍጠር” የሚለውን ቃል ነው። በጥቅሱ ውስጥ “ፍጠር” የሚለውን ቃል በካሬ ቅንፍ ያስቀመጥኩት ለዚያ ነው።

መፍጠርና ማበጀት፦ ማበጀትና መፍጠር በተለዋዋጭነት ሊውሉ አይችሉም ለሚልና፣ ጃፒ ላቀረበው “የተበጀው የአዳም ስጋ ነው የተፈጠረው ግን መንፈሱ ነው” ለሚለው ነጥብ አጭሩና ቀላሉ መልስ ዘካ 12፥1 ላይ ይገኛል፦ ሰማያትን የዘረጋ፥ ምድርንም የመሠረተ፥ የሰውንም መንፈስ በውስጡ የሠራ [ያበጀ] እግዚአብሔር እንዲህ ይላል” አማርኛው የሰራ ብሎ ያስቀመጠው ቃል በዘፍ2፥7 ላይ ከዋለው “ማበጀት” ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል ጋር አንድ ነው ለዚህም ነው በካሬ ቅንፍ “ያበጀ” የሚለውን ቃል ያስገባሁት። ይህ ክፍል መንፈስን ፈጠረ ሳይሆን አበጀ ማለቱ “የተፈጠረው መንፈስ ነው፣ የተበጀው ደግሞ ስጋ ነው” ከሚለው ትምህርት ጋር በቀጥታ የሚቃረን ነው።  የፍጥረትን ጅማሬ በሚተርክ በዚህ የዘካርያስ ክፍል “የሰውን መንፈስ በውስጡ ያበጀ” ማለቱ ደግሞ መንፈስ ከስጋ ቀድሞ እንደመጣ አድርጎ ከሚያቀርበው አስተምህሮ ጋር የማይስማማ ነው፣ ያለስጋ “ውስጥ” የለምና። “የሰውንም መንፈስ” እና “በውስጡ” የሚሉ አገላለጾችን በመጠቀሙ ደግሞ መንፈስ ራሱን ችሎ “ሰው” የሚባል ነገር ሳይሆን እንደ አንድ የሰው ክፍል የሚታይ አድርጎ ስለሚያቀርበው “እግዚአብሔር ሰው ብሎ የሚጠራው መንፈስን ነው” የሚለው አስተምህሮ ምን ያህል ብዙ የመጽሃፍ ቅዱስ ክፍሎችን ግንዛቤ ውስጥ ያላስገባ አስተምህሮ እንደሆነ የሚያሳይ ነው። “ማበጀት” የሚለው ቃል ያለ ነገርን ተጥቅሞ ማበጃጀት ብቻ እንዳልሆነ ደግሞ የሚያሳየን በኢሳይያስ 43፥10 ያለው ክፍል ነው፦ “ከእኔ በፊት አምላክ አልተሠራም [አልተበጀም] ከእኔም በኋላ አይሆንም።” አማርኛው አልተሰራም ያለው ቃል አሁንም በዕብራይስጡ በዘፍ 2፥7 ላይ ያለው “ማበጀት” የሚለው ቃል ነው። ከእግዚአብሔር በፊት ምንም ነገር የለም፣ ምንም አምላክም የለም። እንደ ጃፒ ትርጉም ከሆነ ደግሞ ከምንም ነገር የሆነን ነገር ማስገኘት “መፍጠር” እንጂ “ማበጀት” ሊሆን ስለማይችል “ከእኔ በፊት አምላክ አልተበጀም” ማለቱ ስህተት ነው ልንል ነው ማለት ነው። ከምንም ነገር በፊት፣ ከራሱ ከእግዚአብሔር እንኳን በፊት “አልተበጀም” የሚለውን ቃል መጠቀሙ፣ እስራኤላዊያን ሆኑ ነቢያቱ ጃፒና ሌሎች ይህን ትምህርት የሚያስተምሩ ሰዎች የቃሉ ትርጉም እንዲህ እና እንዲያ ብቻ ነው እያሉ በሚያስቅምጡት መልኩ እንደማያዩት አመላካች ነው። ሌላው “ፈጠረ”ና “አበጀ” በተለዋዋጭነት መዋልቸውን የሚያሳየን ክፍል ደግሞ ኢሳ 43፥7 ነው፦ “ሰሜንን፦ መልሰህ አምጣ፥ ደቡብንም፦ አትከልክል፤ ወንዶች ልጆቼን ከሩቅ ሴቶች ልጆቼንም ከምድር ዳርቻ፥ በስሜ የተጠራውን ለክብሬም የፈጠርሁትን፥ የሠራሁትንና ያደረግሁትን [ያበጀሁትን] ሁሉ አምጣ እለዋለሁ።” ይህ ክፍል የእግዚአብሔርን ህዝብ “ለክብሬ የፈጠርኩት፣ የሰራሁትና ያበጀሁት” በማለት ሶስቱንም ቃላት አንድ ድርጊትን ለመግለጽ መጠቀሙ ሶስቱም ቃላት በብሉይ ኪዳን ፀሃፊዎች ዘንድ በተለዋዋጭነት ይውሉ እንደነበረ በግልጽ የሚያሳይ ክፍል ነው6። በኢሳ 45፥18ም “ሰማያትን የፈጠረ እግዚአብሔር፥ እርሱም ምድርን የሠራና ያደረገ [ያበጀ] ያጸናትም፥ መኖሪያም ልትሆን እንጂ ለከንቱ እንድትሆን ያልፈጠራት [ባዶ እንድትሆን ያልፈጠራት፥ የሰው መኖሪያ እንድትሆን ያበጃት] አምላክ፥ እንዲህ ይላል፦ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ከእኔም በቀር ሌላ የለም።” በካሬ ቅንፍ ያሰገባኋቸው ቃላት የዕብራይስጡን ሃሳብ ሳይሸረፍ እንዳለ ለማስቀመጥ ነው። እንዲሁም ኢሳ 45፥7፦ “ብርሃንን ሠራሁ [አበጀሁ] ጨለማውንም ፈጠርሁ ደኅንነትን እሠራለሁ [አበጃለሁ] ክፋትንም እፈጥራለሁ እነዚህን ሁሉ ያደረግሁ እግዚአብሔር እኔ ነኝ” በማለት “መፍጠር”ና “ማበጀት” በነቢያቱ ዘንድ በተለዋዋጭነት ጥቅም ላይ ይውሉ እንደነበር ክፍሉ ያሳይናል። ብርሃንን በዘፍ 1፥3 ላይ “ይሁን” ብሎ ቢፈጥረውም እዚህ ላይ “አበጀሁት” ይለናል፤ እንዲሁም በኢሳ 45፥7 “ክፋትን እፈጥራለሁ” ቢለም በኤር 18፥11 “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ክፉ ነገር እፈጥርባችኋለሁ [አበጅባችኋለሁ] አሳብንም አስብባችኋለሁ” ክፉ ነገርን “አበጅባችኋለሁ” ማለቱ የቃላቱን ተወራራሽነት (interchangeability) ያሳያል።

ይህ ሁሉ እንግዲህ በየትኛውም አውድ የሶስቱ ቃላት ትርጓሜ “አንድ እና አንድ ነው” ለማለት ሳይሆን፣ የብሉይ ኪዳን ጸሃፊዎች ቃሎቹን በተለዋዋጭነት እንዴት እንደተጠቀሟቸውና ጃፒ የሰጠው ትርጉም ከእነዚህ አጠቃቀሞች ጋር የሚጣረስ እንደሆነ ለማሳየት ነው።

የአፈታት ቀውስበጃፒ አፈታት ላይ ከላይ ያቀረብኳቸውን ቋንቋዊና መጽሃፍ ቅዱሳዊ ትችቶች ወደ ጎን ትተን እስኪ የ “ሰው መንፈስ ነው” አስተማሪዎች የሚፈቱበትን መንገድ መከተል የሚያመጣውን የአፈታት ቀውስ እንመልከት። ዘፍጥረት 1 እና 2ን በተመለከተ ሰፊ ተቀባይነት ያለው አረዳድ እንደሚከተለው ነው፦ ምዕራፍ 1 የሁሉንም ፍጥረት ጅማሬ በአጭሩ የሚተርክ ነው፤ ምዕራፍ 2 ደግሞ በክለሳ መልኩ በስድስተኛው ቀን ላይ የተከናወነውን የእግዚአብሔርን የመፍጠር ስራ ዘርዘር አድርጎ የሚያቀርብ ነው። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት፦ ምዕራፍ 1 እንደ ዜና ርዕሰ አንቀጽ ሲሆን ምዕራፍ 2 ደግሞ የ6ኛው ቀን ርዕሰ አንቀፅ ዝርዝር ዘገባ ነው ማለት ይቻላል። ጃፒ የሚለው ግን ምዕራፍ 2 የምዕራፍ 1 ክለሳ ወይም ዝርዝር ሳይሆን ራሱን የቻለ ከ6ቱ ቀን የፍጥረት ስራ የቀጠለ ሌላ ዘገባ ነው ባይ ነው። እንዲህ ያለውን አፈታት ከተከተልን የሚገጥመንን ችግር በአጭሩ ልዘርዝር፦

  • ዘፍ 2፥1 “ማይና ምድር ሠራዊታቸውም ሁሉ ተፈጸሙ።” እያለ እኛ “አይ አልተፈጸመም” እንድል ያደርገናል።
  • እግዚአብሔር ከፈጠረውና(created) ከሰራው(made) ስራ ሁሉ አረፈ ካለ በኋላ ሌላ የመፍጠርና የመስራት ስራ ውስጥ መግባቱ። ምክንያቱም በምዕራፍ ሁለት ላይ ሰማይና ምድር ስለመፈጠራቸውና ስለመሰራታቸው፣ ሰው ስለመበጀቱ፣ እንስሳት ስለመሰራታቸውና ሴት ስለ መሰራቷ ያወራልና።
  • ዘፍ2፥5 “እግዚአብሔር አምላክ ሰማይንና ምድርን ባደረገ [በሰራ] ቀን፥ በተፈጠሩ ጊዜ የሰማይና የምድር ልደት ይህ ነው።” ያለውን ሃስብ እንደክለሳ ካላየነው በቀር የዘፍጥረት ምዕራፍ አንዱ ሰማይና ምድር ከዘፍጥረት ምዕራፍ ሁለቱ ሰማይና ምድር የተለየ አድርገን እንድናስብ ማስገደዱ። እግረ መንገዳችንን መስራትና መፍጠርን እንዴት በተለዋዋጭነት እየተጠቀመባቸው እንደሆነ ልብ እንበል።
  • ዘፍ2፥7 “ሰውን ከምድር አፈር አበጀው” የሚለውን እንደ ዘፍ 1፥27 ዝርዝር ክለሳ ካላየነው በቀር የምዕራፍ አንዱ ሰው ከምዕራፍ ሁለቱ ሰው ይለያል ብለን እንድናስብ ማስገደዱ። አይ ይሄ ለተፈጥረው መንፈስ ስጋ መበጀቱን ነው የሚያሳይ ማለት በማንችልበት መልኩ በግልጽ ቋንቋ “የሰውን ስጋ” ሳይሆን ራሱ ሰውን ከአፈር አበጀው ማለቱን ልብ እንበል፣ እንዲያ ከሆነ ደግሞ መንፈስ የሆነ ሰው ዘፍጥረት 1፥27 ላይ ተፍጥሯል ሌላ ሰው ደግሞ ከአፈር 2፥7 ተፈጥሯል ማለት ነው።
  • ዘፍ1፥27 የሚያውራው መንፈስ የሆነ ሰው ስለመፈጠሩ ብቻ ከሆነ፣ “ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠረው” ስለሚል መንፈስ ጾታ አለው እንድንል ያስገድደናል፣ “ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሏት ግዟትም” የሚለው ደግሞ መንፈስ ይዋለዳል ደግሞም ምድርን መሙላት ይችላል እንዲሁም እንስሳትን መግዛት ይችላል እንድንል ያስገድደናል። “አይ ይሄ በረከት እግዚአብሔር አዳም ወደፊት ስጋ መልበሱን አይቶ የተናገረው ነው” የሚል መከራከሪያ ይቀርብ ይሆናል፣ ነገር ግን እግዚአብሔር ከቁጥር 28 በፊት በቁጥር 22 ላይ በእንዲህ ያለ በረከት የባረካቸውን እንስሳት ስናይ ለመራባት የሚያስፈልጋቸውን ጾታና ቦታ (ውሃና ሰማይ) ሰጥቶ ስለሆነ ሰውንም ያንን በረከት ሲባርከው መራባት የሚችልበትን ጾታና መሬት ሰጥቶ ሊሆን ይገባዋል።
  • ዘፍ 1፥29 “እግዚአብሔርም አለ፦ እነሆ መብል ይሆናችሁ ዘንድ በምድር ፊት ሁሉ ላይ ዘሩ በእርሱ ያለውን ሐመልማል ሁሉ፥ የዛፍን ፍሬ የሚያፈራውንና ዘር ያለውንም ዛፍ ሁሉ ሰጠኋችሁ” ማለቱ ደግሞ መንፈስ እንደ አራዊትና የምድርን ሐመልማል መብላት ይችላል እንድንል ያስገድደናል።
  • ምዕራፍ 2ን እንደክለሳ ካላየነው የተፈጠሩትን እንስሳት ሁለት ጊዜ ማለትም አንዴ በዘፍ 1፥25 ሌላ ጊዜ ደግሞ በዘፍ 2፥19 ላይ ፈጥሯል እንድንል ያስገድደናል ወይም የዘፍ 1፥25 እንስሳት መንፍስት ናቸው ስለዚህም “በእግዚአብሔር መልክ” ናቸው በ2፥19 ላይ ስጋ እየለበሱ ነው እንድንል ያስገድደናል።

ከላይ እንዳሳየሁት መፍጠርና ማበጀት በሚሉት ቃላት ላይ ጃፒ የሰጠው ትርጉም ፈጽሞ ከብሉይ ኪዳን ጸሃፊዎች የቃላቱ አጠቃቀም ጋር፣ ከምንኖርበት ማህበረሰብ የቃላቱ አጠቃቀም ጋርና የተለያዩ መዝገበ  ቃላት ከሚሰጡት ትርጓሜ ጋር አብሮ የማይሄድ ነው፣ እንዲሁም ዘፍጥረት ምዕራፍ አንድንና ሁለትን ለመፍታት የተከተለው አፈታት አጠቃላይ ክፍሉን ቀውስ ውስጥ የሚከት አፈታት ነው።

3. የተውላጠ ስሞች አጠቃቀም 

በዚህ የመካራከሪያ ነጥቡ ጃፒ የሚለው ይህን ነው፦ እግዚአብሔር ወይም መጽሃፍ ቅዱስ መንፈስንና ሰውን በተለዋዋጭነት (interchangeably) ስለሚጠቀምባቸው እግዚአብሔር ወይም መጽሃፍ ቅዱስ “ሰው” የሚለው መንፈስን ነው። ወይም መጽሃፍ ቅዱስ መንፈስንና ሰው-አመልካች-ተውላጠ-ስሞችን (እኔ፣ አንተ፣ አንቺ፣ እሷ፣ እሱ፣ እናንተ) በተለዋዋጭነት ስለሚጠቀምባቸው መጽሃፍ ቅዱስ “ሰው” ሲል መንፈስን ማለቱ ነው።

ለዚህ መከራከሪያ መልስ ለመስጠት በመቶዎችችና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰው-አመልካች-ተውላጠ-ስሞችን ከሰው መንፈስ ጋር ሳይሆን ከሰው ስጋ ጋር በተለዋዋጭነት የሚጠቀሙ ጥቅሶችን ማቅረብ ይቻላል። በሁለተኛው ነጥብ በአጭሩ እንዳብራራሁት አማርኛው “ስጋ ለባሽ” ወይም “ስጋ የለበሰ” እያለ የተርጎማቸው በዕብራይስጡና በግሪኩ “ስጋ” ተብለው የተቀመጡ ሲሆን እነዚህንም ጥቅሶች ወስድን እግዚአብሔር “ሰው” እና “ስጋ”ን በተለዋዋጭነት ስለተጠቀመባቸው ሰው ስጋ ብቻ ነው ልንል እንችላለን። በነገራችን ላይ ይህንኑ ዓይነት መከራከሪያ “ሰው ስጋ ብቻ ነው” ለማለት የሚጠቀሙ ብዙ ሃይማኖቶችና አስተማሪዎች አሉ። ጃፒ የጠቀሳቸውን ጥቅሶች ከማየታችን በፊት እስኪ ስለ ተውላጠ ስም አጠቃቀም ጥቂት ማብራሪያ ከምሳሌ ጋር ልስጥ።

“እሱ እሷን በቦክስ ሲመታት ደም በደም ሆነች” ብሎ አንድ ሰው ስለ አንድ አጋጣሚ ነገረን እንበል። ያንኑ ሁኔታ ያየ ሌላ ሰው “እሱ አፍንጫዋን በቦክስ ሲመታት አፍንጫዋ ደም በደም ሆነ” ብሎ ሲናገር ደግሞ ሰማን እንበል። ሁለተኛው አገላለጽ ከመጀመሪያ የሚለየው አፍንጫ የሚል ቃል መጨመሩ ሲሆን የሚያስተላልፉት ሃሳብ ግን አንድ አይነት ነው። የመጀመሪያው ተናጋሪ “አፍንጫዋን” የሚለውን ቃል “እሷ” ብሎ ስለተካውና አፍንጫዋንና እሷን በተለዋዋጭነት ስለተጠቀመ እሷ ማለት አፍንጫዋ ናት አንልም። ወይም አንድ ሰው መጀመሪያ “አመመኝ” ብሎን ቀጥሎ “ራሴን አመመኝ” ቢለን “የእኔን ራስ” እና “እኔን” የሚሉትን ቃላት በተለዋዋጭነት ስለተጠቀመ ሰውየው ራስ ነው አንልም። እንዲህ ዓይነት የተውላጠ ስም አጠቃቀም ያለምንም ችግር በስፋት በዕለት-ተዕለት ኑሯችን እንጠቀማለን፣ መጽሃፍ ቅዱስም ይጠቀማል። የወሬው አውድ ስለሚገባን “እሷ” የሚለው የሚያመለክተው “አፍንጫዋን” እንደሆነ እንገነዘባለን እንጂ “እሷ ማለት አፍንጫዋ ናት” አንልም፣ እንዲሁም “እኔን” የሚለውን ቃል “ራሴን” ከሚለው ጋር በተለዋዋጭነት ስለተጠቀምንበት ሰውየው “እኔ” ብሎ የሚጠራው ወይም “ሰው” ብሎ የሚጠራው ራስን (head) ነው አንልም። ይህ እንግዲህ ተውላጠ ስም እንደ አውዱ አንዳንዴ ሙሉ ሰውን ሲያመለክት ሌላ ጊዜ ደግሞ የሰውን አንድ ነገሩን ወይም ክፍሉን ያመለክታል ለማለት ነው።

እስኪ የዚህ ዓይነት አጠቃቀም በዘፍጥረት ዘገባ ውስጥ እንመልከት። ዘፍ 2፥22 “ከአዳም የወሰዳትን አጥንት ሴት አድርጎ ሠራት” በማለት ሴት የተገኘችው ከአዳም አጥንት እንደሆነ ይነግረንና መልሶ ግን በቁጥር 23 ላይ “እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል” በማለት ሴት ከወንድ አጥንት ሳይሆን ከወንድ ተገኝታለች ይለናል። ይህን ስናይ የወንድን አጥንት በ“ወንድ” ስለተካው ለመጽሃፍ ቅዱስ ወይም ለእግዚአብሔር ወንድ ማለት አጥንት ነው አንልም። “ከወንድ” ሲል አጥንትን ለይቶ ወንድ እያለው እንዳልሆነ ግልጽ ነው፣ “ከወንድ” ሲል “ከወንድ አጥንት” እንደሆነ ከአውዱ እንረዳለን።

ወደ ጃፒ አፈታት ስንመለስ የእሱ መከራከሪያ “ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህ” የሚለው አነጋገር ወይ “ከእርሱ በበላህ ቀን መንፈስህ ሞትን ይሞታል” ማለት ነበረበት ወይ መጽሃፍ ቅዱስ “አንተ” እያለ የሚጠራው መንፈስን ነው ባይ ነው። እኔ ደግሞ ከላይ በሰጠሁት ማብራሪያ መሰረት ይህ አፈታት አያስኬድም ባይ ነኝ። በዚህ አካሄድ ከሆነ ጃፒ “አዳም በስጋው ሞቷል እንዴ?” የሚል መከራከሪያ እንዳቀረበ ሌላም ሰው በቀላሉ “አዳም በመንፈሱ በልቷል እንዴ?” የሚል መከራከሪያ ሊያነሳና “[አንተ] በበላህ” በሚለው ንግግር ውስጥ ያለው “አንተ” የሚያመለክተው ስጋውን ስለሆነ እግዚአብሔር “አንተ” ወይም “ሰው” የሚለው ስጋን ነው ሊል ይችላል። እንዲህ ያለ የጸጉር ስንጠቃ አፈታት እንደማያስኬድ እስኪ ጃፒ በሚለው መንገድ ተጨማሪ የዘፍጥረት ምዕራፍ 2 ክፍሎችን እየተረጎምን እንያቸው፦

  • ዘፍ 2፥21 “እግዚአብሔር አምላክም በአዳም ከባድ እንቅልፍን ጣለበት፥ አንቀላፋም፤ ከጎኑም አንዲት አጥንትን ወስዶ ስፍራውን በሥጋ ዘጋው።” እዚህ ላይ “መንፈስ ያንቀላፋል እንዴ?” ብለን ብንጠይቅ “አይ የለም የሚያንቀላፋው ስጋ ነው” የሚል መልስ እናገኛለን። ከዚያም በመነሳት “[እርሱ] አንቀላፋም” ስለሚል እግዚአብሔር “እርሱ” የሚለው ስጋን ነው ስለዚህም “ሰው” የሚለው ስጋን ነው ልንል እንችላለን።
  • ዘፍ 2፥22 “እግዚአብሔር አምላክም ከአዳም የወሰዳትን አጥንት ሴት አድርጎ ሠራት” በተመሳሳይም “መንፈስ አጥንት አለው እንዴ?” በማለት እግዚአብሔር “አዳም” እያለ የሚጠራው ስጋን ነው ልንል እንችላለን፣ ስጋ እንጂ መንፈስ አጥንት የለውምና።
  • ዘፍ 2፥25 “አዳምና ሚስቱ ሁለቱም ዕራቁታቸውን ነበሩ፥ አይተፋፈሩም ነበር።” እንዲሁም “መንፈስ ራቁቱን ነው ይባላል እንዴ?” በማለት “[እነርሱ] ዕራቁታቸውን ነበሩ” ስለሚል፣ እግዚአብሔር “አዳምና ሔዋን” ወይም “እነርሱ” ወይም “ሰው” እያለ የሚጠራው ስጋን ነው ልንል እንችላለን።

የዚህ ዓይነት በመቶዎችና በሽዎች  የሚቆጠሩ ጥቅሶችን እያወጣን ልናይ እንችላለን፣ ቁም ነገሩ ግን – ተውላጠ ስሞች ከሆነ የሰው ክፍል ጋር በተለዋዋጭነት ስለዋሉ፣ ያ የሰው ክፍል ብቻ ነው “ሰው” ማለት አያስኬድም የሚለው እውነታ ነው።

ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነው

ከዚህ ሶስተኛው ነጥቡ ጋር አያይዞ ጃፒ የሚያነሳው የመጽሃፍ ቅዱስ ክፍል በዮሃንስ ወንጌል 3፥1-8 ያለውን በኒቆዲሞስንና በኢየሱስ መካከል ያለውን ውይይት ነው። ኢየሱስ “ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር” ማለቱ የሰውን መንፈስነት የሚያሳይ አባባል ነው ባይ ነው። ምክንያቱሳ ካላችሁ፦ ስጋ ዳግመኛ ሊወለድ አይችልም፣ የሚወለደው መንፈስ ነው፣ ስለዚህ ኢየሱስ “ሰው” እና “መንፈስ”ን በተለዋዋጭነት እየተጠቀመ ነው፣ በተለዋዋጭነት ከተጠቀማቸው ደግሞ ሰው ማለት መንፈስ ነው ይሆናል የጃፒ ምላሽ። ከዚያም “ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነው” ስለሚል በኢየሱስ ያመንን እኛ መንፈስ ነን በማለት ሃሳቡን ያጠናክራል። ኒቆዲሞስም “ሰው ከሸመገለ በኋላ” ሲል ከኢየሱስ በተቃረነ መልኩ “ሰው ብሎ define ያደረገው ሽማግሌ፣ ሽበታም ሰውየ ነው” ይለንና “በኢየሱስ ስም … እንዲህ ዓይነት የኒቆዲሞስን እይታ ከምድሪቱ ላይ አንስቻለሁ” ብሎ ያውጃል። የዚህ ዓይነቱ አፈታት ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት የተውላጠ ስምን አጠቃቀም ካለመረዳት ወይም “ሰው” የሚለውን ቃል ከመንፈስ ጋር በተለዋዋጭነት መዋሉን “ሰው መንፈስ ለመሆኑ ማሳያ ነው” ከሚለው የተሳሳተ ግንዛቤ የሚነሳ ነው። (በነገራችን ላይ ይህ የዮሃንስ ወንጌል ክፍል ሰውና መንፈስን በተለዋዋጭነት እየተጠቀመ አይደለም፣ እንዴት እንዳልሆነም ወደኋላ አሳያለሁ።)  “ሰው” የሚለው ቃል ከመንፈስ ጋር ብቻ ሳይሆን ከስጋም ጋር በተለዋዋጭነት በብዙ የመጽሃፍ ቅዱስ ክፍሎች ላይ ዉሏል፣ ነገር ግን እነዚህኛዎቹ ክፍሎች “ሰው ስጋ ነው” ሊያስብሉን እንደማይችሉ ሁሉ እነዚያኛዎቹ ክፍሎች ደግሞ “ሰው መንፈስ ነው” አያስብሉንም። ለምሳሌ 1ቆሮ 2፥11 “በእርሱ ውስጥ ካለው ከሰው መንፈስ በቀር ለሰው ያለውን የሚያውቅ ሰው ማን ነው?” በማለት  ከመንፈሱ-ውጭ-ያለውን-የሰው-ክፍል ራሱን አስችሎ “ሰው” በማለቱ መንፈስ ለሰው ተጨማሪ ነገር እንጂ ሰውን ሰው የሚያስብለው መንፈሱ አይደለም ልንል ነው ማለት። ይህ ከሰው ቋንቋ ውስንነት የመጣ አገላለጽ ነው እንጂ “ሰው” የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ ከመንፈሱ ነጥሎ እያየው አይደለም። እንደዛ ከሆነ “በልሳን ብጸልይ መንፈሴ ይጸልያል አእምሮዬ ግን ያለ ፍሬ ነው። እንግዲህ ምንድር ነው? በመንፈስ እጸልያለሁ በአእምሮም ደግሞ እጸልያለሁ፤ በመንፈስ እዘምራለሁ በአእምሮም ደግሞ እዘምራለሁ።” የሚለውን ጥቅስ ሰው ከመንፈሱም ከአእምሮውም ውጭ የሆነ ሌላ “ሰው” የሚባል ክፍል አለው ልንል ነው ማለት ነው። ነገሩን ደግሞ የበለጠ ግልጽ ለማድረግ 1ተሰ 5፥ 23ን ልንጠቅስ እንችላለን፦ “መንፈሳችሁም ነፍሳችሁም ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ” ከዚህ ጥቅስ ተነስተን “[የእናንተ] መንፈስ፣ [የእናንተ] ነፍስ፣ [የእናንተ] ስጋ” ስላለ፣ “እናንተ” እያለ የሚጠራው ከመንፈስ፣ ከነፍስና ከስጋ ውጭ የሆነ ክፍል አለ ልንል ነው ማለት ነው። ምክንያቱም እንደ ጃፒ አፈታት ከሆነና ሰው መንፈስ ከሆነ “እናንተም፣ ነፍሳችሁም፣ ስጋችሁም” ሊባል ይገባው ነበር፣ እንደ ጃፒ አፈታት ከሆነና ሰው ደግሞ ነፍስ ከሆነ “መንፈሳችሁም፣ እናንተም፣ ስጋችሁም” ሊባል ይገባው ነበር፣ እንዲሁም እንደ ጃፒ አፈታት ከሆነና ሰው ስጋ ከሆነ ደግሞ “መንፈሳችሁም፣ ነፍሳችሁም፣ እናንተም” ሊባል ይገባው ነበርና ነው። ጳውሎስ ግን ማለት የፈለገው “[እናንተን ይቀድስ፣ እናንተን ስልም መንፈሳችሁን፣ ነፍሳችሁንና ስጋችሁን ማለቴ ነው]” ነው።

“ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር” የሚለው የኢየሱስ አባባል “ሰው መንፈስ ነው” ብሎ እንደሚያምን ማሳያ ነው የሚለውን ለመመለስ እስኪ አንድ ምሳሌ እንይ። “ማራዶና ኳሷን መታት” ስንል ማራዶና ከእግር ጥፍሩ እስከ ራስ ፀጉሩ ወይም በመላ ሰውነቱ ኳሷን መታት ማለታችን እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ወይም ደግሞ ይህንን የነገርነው ሰው ማራዶና ኳሷን በእግሩ ስለመታት “ማራዶና ማለት እግሩ ነው” የሚል ድምዳሜ ላይ አይደርስም። ማራዶና ሲነሳ መቼም አውዱ የእግር ኳስ ጨዋታ መሆኑን የሚያውቅ ሰው፣ ኳሷን በእግሩ አልያም በግንባሩ እንጂ በመላው ሰውነቱ መታት ለማለት እንዳልሆነ ይገባዋል። ልክ እንደዚያው “ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር” ሲል አውዱ የሚገባን እኛ “ሰው [በመንፈስ] ዳግሞኛ ካልተወለደ በቀር” ማለቱ እንጂ የሰው ሁለንተና ዳግመኛ ይወለዳል ወይም ማራዶና ማለት እግሩ ነው እንዳላልነው ሁሉ፣ ሰው መንፈስ ነው ለማለት እንዳልሆነ ይገባናል። ኒቆዲሞስም ኢየሱስ እያወራ ያለው ስለምን እንደሆነ ስላልገባው እንጂ “ሰው መንፈስ ነው” የሚለው ትምህርት ስላልገባው አልነበረም አለመግባባቱ የተፈጠረው። እንዲህ ያለው አለመረዳት በኒቆዲሞስ ላይ ብቻ የተፈጠረ አይደለም። ለምሳሌ ኢየሱስ ከዚያው የኒቆዲሞስ ክፍል ከፍ ብሎ በምዕራፍ 2 ላይ “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ” ሲል የሚያውራው ስለ እራሱ አካል እንደሆነ ያልገባቸው ሰዎች የሰለሞንን ቤተ መቅደስ አፍርሼ እሰራዋለሁ ብሏል ብለው ከሰውታል። የኒቆዲሞስ ችግር “ሰው” የሚለውን ያለመረዳት ሳይሆን “ዳግመኛ መወለድ” የሚለውን ያለመረዳት እንደሆነ የክፍሉ አውድ በግልጽ ያሳየናል። ራሱ ኢየሱስ በዮሃ 21፥18 “እውነት እውነት እልሃለሁ፥ አንተ ጐልማሳ ሳለህ ወገብህን በገዛ ራስህ ታጥቀህ ወደምትወደው ትሄድ ነበር፤ ነገር ግን በሸመገልህ ጊዜ እጆችህን ትዘረጋለህ፥ ሌላውም ያስታጥቅሃል ወደማትወደውም ይወስድሃል አለው።” በማለት ጴጥሮስን አንዴ ጎልማሳ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሽማግሌ ብሎ እንደጠራው ማየቱ በኢየሱስ የ“ሰው” ትርጉም ውስጥ ስጋ የለም የሚለውን አባባል የሚያከሽፍ ነው። ኢየሱስ “ሰው” ሲል ፈጽሞ ስጋን የማያስብ ከሆነ “በስጋ ጎልማሳ ሳለህ … በስጋ በሸመገልህ ጊዜ” ሊለው ይገባ ነበር። እንዲሁም ኢየሱስ በሉቃ 24:6-7 “የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ አልፎ ሊሰጥና ሊሰቀል በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ግድ ነው” በማለት እንደሚሰቀልና ከሞት እንደሚነሳ፣ በሌሎች ክፍሎችም እንደሚቀበር ተናግሯል። ታዲያ እንደምናውቀው መንፈስ አይሰቀልም፣ አይቀበርም ወይም ከመቃብር አይነሳም። ኢየሱስ “ሰው” ሲል መንፈስን ብቻ ከሆነ የሚያስበው “የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ አልፎ ሊሰጥና ስጋው ሊሰቀል በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ግድ ነው”  ሊል ይገባው ነበር።  እዚህ ላይ ማስታዎስ ያለብን ይህ አባባሉ “ሰው ስጋ ነው” የሚለውን ትምህርትም ለማስተላለፍ የታሰበ እንዳልሆነ ነው። ጉልምስናና ሽምግልና ሲነሳ አውዱ የስጋ አውድ እንደሆነ ግልጽ ስለሆነ ኢየሱስ “በስጋህ” የሚለው ቃል መጨመር አያስፈልገውም እንዲሁም “ዳግም ካልተወለደ” ሲል የሚያወራው ስለመንፈስ እንደሆነ ግልጽ ስለሆነ “በመንፈስ” የሚለውን ቃል መጨመር አላስፈለገውም። በእርግጥ ኒቆዲሞስ አውዱ እንዳልገባው ሲያውቅ ኢየሱስ የሚያውራው ስለመንፈስ እንጂ ስለስጋ እንዳልሆነ አስረድቶታል።

“ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነው” የሚለውም ሃሳብ “ዳግመኛ የምትወለደው ከመንፈስ ስለሆነና ከመንፈስ የሚወለድ ደግሞ መንፈስ ስለሆነ፣ ዳግመኛ የሚወለደው መንፈስህ ነው” ለማለት ነው እንጂ ሰው መንፈስ ነው ወይም ይሆናል ለማለት አይደለም። ዮሃንስ ከኢየሱስ ትምህርት “ሰው መንፈስ ነው” የሚለውን አግኝቶ ቢሆን ወንጌሉን ሲጽፍ በምዕራፍ አንድ ላይ “ቃልም ስጋ ለበሰ” እንጂ “ቃልም ስጋ ሆነ” ሊል አይገባውም ነበር። “ከስጋ የተወለደ ስጋ ነው” የሚለውም ሃሳብ ከስጋ ሁለተኛ መወለድ አይቻልም ቢቻልም እንኳ ስጋ የሚወልደው መልሶ ስጋን ስለሆነ መንፈሳዊ ለሆነው ዳግመኛ መወለድ የሚፈይደው ነገር እንደሌለ ለማሳየት እንጂ ከመንፈስ የሚወለዱ ሰዎች ስጋነታቸው ቀርቶ መንፈስ ይሆናሉ ማለት እንዳልሆነ ግልጽ ነው። የሰጠሁት ማብራሪያ አሳማኝ ሆኖ ካልተገኘ እስኪ መለስ ብለን ሌላኛውን አማራጭ ፍች ማለትም በዚህ ክፍል ላይ የሰጠውን የጃፒን ፍች መከተል የሚያመጣውን የአፈታት ቀውስ እንመልከት፦

  1. “ከስጋ የተወለደ ስጋ ነው፣ ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነው” የሚለውን ወንድማችን ጃፒ በሚለው ዓይነት አረዳድ ከተረዳነው ኒቆዲሞስ ስጋ ነበረ ማለት ነው። ለምን? ከመንፈስ ስላልተወለደ፣ የተወለደው ገና ከስጋ ብቻ ስለሆነ። ኒቆዲሞስ ስጋ ከሆነና ኢየሱስ ደግሞ ሰው ሲል መንፈስን ማለቱ ከሆነ “ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር” ማለት አልነበረበትም፣ እንዲሁም ጸሃፊው በቁጥር አንድ ላይ “ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ” ማለት አልነበረበትም። ለምን? ዳግም ያልተወለደ ሰው ከመንፈስ አልተወለደም፣ ከመንፈስ ካልተወለደ ደግሞ ስጋ እንጂ መንፈስ አይደለም፣ መንፈስ ደግሞ ካልሆነ “ሰው” ሊባል አይገባውምና። በተጨማሪም ጃፒ “ሰውየው ዳነም አልዳነም spirit being ነው”7 ካለው ጋር እንዲሁም “ሰው መንፈስ ነው” ነው ለሚለው አስተምህሮ ዋና መከራከሪያ ከሆነው፣ ሰው መንፈስ የሆነው ገና ከፍጥረቱ በእግዚአብሔር መልክ በመፈጠሩ እንጂ ዳግም በመወለዱ አይደለም ከሚለው መከራከሪያ ነጥብ ጋር የሚቃረን ነው።
  2. ሰው ዳግም ባይወለድም መንፈስ ነውና “ሰው” ተብሎ ሊጠራ ይችላል የሚል ክርክር ይነሳ ይሆናል። ይህ ግን የ“ሰው መንፈስ ነው” አስተማሪዎች “ከስጋ የተወለደ ስጋ ነው፣ ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነው” የሚለውን ከሚፈቱበት መንገድ ጋር በቀጥታ የሚጣረስ ነው። በተጨማሪም ሰው ዳግም ሳይወለድም መንፈስ ከሆነ ታዲያ የዳግም መወለድ ጥቅሙ ምንድን ነው ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል፣ ምክንያቱም በጃፒ አፈታት መሰረት ዳግም መወለድ ማለት መንፈስ መሆን ማለት ስለሆነ።
  3. ኢይሱስ “ሰው” ሲል የሚያረጀውንና የሚሸብተውን ሰውነቱን የማይጨምር ከሆነ፣ “ሰው ዳግም ካልተወለደ በቀር” በሚለው ቃል ውስጥ ዳግም የሚለውን ቃል ማስገባት አልነበረበትም። ለምን? ዳግም ማለት ሁለተኛ ማለት ነው፣ ኢየሱስ እያለው ያለው መወለድ ደግሞ ሁለተኛ የሆነው የስጋው መወለድ እንደ አንደኛ መወለድ ተቆጥሮ ነው። ሰው ስንል መንፈስ ማለት ከሆነ ግን ስለስጋው መወለድ ልናወራ አንችልም፣ ስለዚህም ኢየሱስ የሚለው መወለድ የመጀመሪያ መወለድ እንጂ ሁለተኛ መወለድ ሊሆን አይችልም። እዚህ ላይ ኢየሱስ ራሱ በዚያው ዮሃንስ ምዕራፍ 3 ላይ “ከመንፈስ” የሚለውን ቃል በተጠቀመበት ቦታ ሁሉ “ዳግም” የሚለውን ቃል እንዳልተጠቀመ ልብ እንበል። በዚህ መሰረት ኢየሱስ “ሰው” የሚለውን ቃል “መንፈስ” ከሚል ቃል ጋር በተለዋዋጭነት እየተጠቀመበት ከነበረና “ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነው” ለሚለው ጃፒ የሰጠውን ፍች ከተቀበልን ልክ “ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር” እንዳለው መንፈስ አንዴ እንጂ ዳግመኛ ሊወለድ አይችልምና “ዳግሞ” የሚለውን ቃል አውጥቶ  “ሰው ካልተወለደ በቀር” ሊል ይገባው ነበር።

በአጭሩ ለማለት የፈለኩት፣ የ“ሰው መንፈስ ነው” አስተማሪዎች ለዮሃንስ 3 የሚሰጡትን አፈታት ከተቀበልን “ሰው ዳግም ካልተወለደ በቀር” የሚለው የኢየሱስ አባባል ራሱ “ሰው መንፈስ ነው” የሚለውን ትምህርት ያልተከተለ ነው ለማለት ነው።

መደምደሚያ 

በመግቢያው እንደገለጽኩት “ሰው መንፈስ ነው” የሚለው ትምህርት እንደኑፋቄ መቆጠር ያለበት ትምህርት ነው ብየ አላስብም። በዚህም ጽሁፍ ላይ ሐዋርያ ብስራት የሰጠውን ትምህርት ወጥነት ባለው መልኩና በቀላሉ ከዩቱዩብ ላይ ስላገኘሁ እንደ መንደርደሪያ ተጠቀምኩ እንጂ ትምህርቱን የሚቀበሉም ይሁኑ የሚያስተምሩ አብዛኞች ሰዎች የሚጠቀሙባቸው የመከራከሪያ ነጥቦች ተመሳሳዮች ናቸው። በዚህ ጽሁፍ ሰው መንፈስ አለመሆኑን ያሳየሁ ሲሆን ይህን ጽሁፍ ለመጻፍ ያነሳሳኝ ዋናው ምክንያት ግን ጃፒ ትምህርቱን ለመደገፍ ያቀረባቸውን ጥቅሶች ለመፍታት የተከተለው አካሄድ ላይ ትልቅ ችግር አለ ብየ ማሰቤ ነው። እንደሚታወቀው ዛሬ “ፕሮቴስታንት”፣ “ጴንጤ ቆስጤ”፣ “ወንጌላዊያን”፣ “ሐዋርያዊ”ና የመሳሰሉት እየተባሉ የሚጠሩት ቤተ እምነቶቻችን መሰረታቸው በ16ኛው ክፍለ ዘመን የተነሳው የተሃድሶ እንቅስቃሴ ነው። የዚህን እንቅስቃሴ አቋሞች የሚያንጸባርቁ “አምስቱ ብቻዎች (five solas)” ተብለው የሚጠሩ መግለጫዎች አሉ። “እምነት ብቻ”፣ “መጽሃፍ ቅዱስ ብቻ”፣ “በክርስቶስ ብቻ”፣ “በጸጋ ብቻ” እና “ክብር ለእግዚአብሔር ብቻ” ተብለው ይታወቃሉ። በእኔ መረዳት “መጽሃፍ ቅዱስ ብቻ” የሚለው አቋም ለሌሎች አቋሞች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እንደ መሰረት የሚያገለግል ከኢየሱስ፣ ከሐዋርያቱና ከቀደሙ የእምነት ወንድሞቻችን የተቀበልነው ትልቅና በጥንቃቄ መያዝ ያለብን ውርሳችን ነው። “መጽሃፍ ቅዱስ ብቻ” የሚለው አዳሾቹ በየትኛውም አስተምህሮ ይሁን ልማድ ላይ መጽሃፍ ቅዱስ ብቻ ባለስልጣን መሆኑን ለማሳየት የተጠቀሙበት አገላለጽ ነው። እንደሌሎች ሃይማኖቶች በትውፊትና የገድል መጻህፍት የታሰርን ባንሆንም አስተምህሯችንን ለመደገፍ ሲባል መጽሃፍ ቅዱስን ከልክ ባለፈ የመጠምዘዝ ባህል ከጊዜ ወደጊዜ እያዳበርን መምጥታችን ግልጽ ነው። በዚህም ምክንያት “መጽሃፍ ቅዱስ ብቻ” የሚለው መሰረታችን ከእኛው የተሃድሶ አራማጆች ነን ከምንለው መሸርሸር እየደረሰበት ይገኛል። እኔም አቅሜ በፈቀደ ይህን መሰረታችንን ለማስጠበቅና ከመሸርሸር ለማዳን በዚህ ጽሁፍ ጥሩ ያልሆኑ የመጽሃፍ ቅዱስ አፈታቶች ናቸው ያልኳቸውን ለማሳየት ሞክሪያለሁ። መጽሐፍ ቅዱስን ከአውዱ በተፋታ መልኩ ቃላቶቹ ላይ በመንጠልጠል ሳይሆን መልዕክቱ ላይ በማተኮር፣ የራሳችንን አስተምህሮ እንዲደግፍልን በመጠምዘዝ ሳይሆን በንፁህ አእምሮ ቃሉ ሊል የፈለገውን በማጤን፣ የተወሰኑ “ተወዳጅ” ጥቅሶችን ብቻ በመደጋገም ሳይሆን ከሌሎችም የመጽሃፍ ቅዱስ ክፍሎች ጋር የሚጣጣመውን ትርጓሜ በመመርመር ልናነበው፣ ልንፈታውና ልናስተምረው ይገባል።

አንዳንድ ሰዎች “ሰው መንፈስ ነው” የሚለውን ትምህርት ከተቀበሉ በኋላ ተለማምደው የማያውቁትን ዓይነት መንፈሳዊ መነቃቃት ስለሚያገኙ፣ መንፈሳዊ መነቃቃቱና እርሱን ተክትሎ የሚመጡትን አንዳንድ በጎ ለውጦች ምንጫቸው “ሰው መንፈስ ነው” የሚለውን ትምህርት ማመናቸው እንደሆነ አድርገው ይቆጥራሉ። ከዚህም የተነሳ በትምህርቱ ላይ ችግር ቢያዩም ወይም መጽሃፍ ቅዱሳዊ መሰረቱ ደካም መሆኑን የሚያሳዩ ፍንጮች ቢያገኙም ትምህርቱን ለመፈተሽ ይሁን ለመጣል ያመነታሉ ወይም ትምህርቱን ጣሉ ማለት እያገለገሉና እየተገለገሉበት ያለውን ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም እየተለማመዱት ያሉትን በጎ ለውጥ አብረው መጣል እንዳለባቸው ያስባሉ። “ሰው መንፈስ ነው” የሚለው ትምህርት ችግሮቹ ከላይ እንዳየነው ሆኖ የሚያስገኘው ግን አንድ ጥቅም ቢኖር፦ ሰው የራሱንና የዙሪያውን ውስንነት ከማየት ለሚመጣ የእምነት እንቅፋት ጆሮውን እንዲደፍን አይኑን እንዲጨፍን ማድረጉ ነው። ይህ ደግሞ ወደ ፅንፍ እስካልተወሰደ ድረስ ለክርስትና አስፈላጊ ነገር ነው። በእኔ እይታ በዚህ አስተምህሮ ውስጥ ያሉ ሰዎች አገኘናቸው የሚሏቸው በጎ ለውጦች ምንጫቸው “ሰው መንፈስ ነው” የሚለው ትምህርት ሳይሆን ይህ በዙሪያ ያለ ሰዋዊና ምድራዊ ተጽዕኖን አልሰማም ብሎ የእግዚአብሔርን ቃል ከራስ ጋር የሚያዋህድ እምነት ነው። ይህን ትምህርት ተቀብለው ላሉ አማኞች የምለው ነገር ቢኖር፦ አሁን ያገኛችሁት መነቃቃት ቢሆን ወይም ፈውስ ወይም የድል ህይዎት፣ ከሰውና ከተፈጥሮ ይልቅ የጌታን ቃል ለማመን ባገኛችሁት አዲስ ድፍረት የመጣ እንጂ “ሰው መንፈስ ነው” የሚለውን ትምህርት ስለተቀበላችሁ አይደለምና ለመጽሃፍ ቅዱስ ታማኝ መሆን አለመሆኑን ለመፈተሽ፣ አለመሆኑንም በተረዳችሁ ጊዜ ትምህርቱን ለመጣል አትፍሩ ነው። እንዲሁም ትምህርቱን መከተል ለማቆም በወሰናችሁ ጊዜ ጥሩ መጽሃፍ ቅዱሳዊ መሰረት ያላቸውን አዳዲስ ልምምዶቻችሁን ይሁን የምትሳተፉባቸውን መንፈሳዊ ህብረቶች አብራችሁ ከትምህርቱ ጋር መጣል እንዳለባችሁ አታስቡ ልል እወዳለሁ።

ለትምህርቱ ዋና ዋና የመከራከሪያ ነጥቦች የሰጠሁት ምላሽ ላላሰመናቸውና “ሰው መንፈስ ነው” የሚለው ትምህርት መጽሃፍ ቅዱሳዊ ነው ለሚሉም የምለው አለኝ። የመጀምሪያው “ሰው መንፈስ ነው” የሚለው ትምህርት የክርስትና መውደቂያና መነሻ ትምህርት አድርገው ከሚያስቡና ከሚያስተምሩ ወገን ከሆናችሁ በእኔ እምነት ወደ ኑፋቄ እየተንደረደራችሁ ነውና መለስ በሉ ማለት እፈልጋለሁ። አንዳንድ ሰዎች ይህን ትምህርት የማይቀበሉ ሰዎችን “ሃይማኖተኛ” ብለው ያንኳስሳሉ፤ “ያለ መንፈስ ቅዱስ ‘ኢየሱስ ጌታ ነው’ ማለት አይቻልም” የሚለውን ጥቅስ “ያለመንፈስ ቅዱስ ‘ሰው መንፈስ ነው’ ማለት አይቻልም” ብለው ሊቀይሩት ነው እንዴ በሚያስብል መልኩ ለትምህርቱ የተጋነነ ቦታ ይሰጣሉ። በእኔ መረዳት ትምህርቱ ከአከራካሪነት ወይም ተራ ስህተት ወደ ኑፋቄነት የሚሻገረው ያኔ ነው። እንዲሁም ትምህርቱን እንደልዩ መገለጥ የሚያቀርቡ ሰዎችም ትምህርቱ ነባርና ተራ እንደሆነ እንዲገነዝቡ እወዳለሁ። ይህ ትምህርት እንደሚባለው መንፈሳዊ ሰዎች ብቻ የሚረዱት ሳይሆን ከክርስትና በእጅጉ ያፈነገጡ እንደ ሳይንቶሎጂ (Scientology)8 እና ሞርሞኒዝም (Mormonism)9 ያሉ ሃይማኖቶችም በስፋት የሚያስተምሩት ነው። በግርጌ ማስታዎሻዎች የተሰጡትን ድረ-ገፆች መመልከት ይቻላል። ይህን የምለው እነዚህ ሃይማኖቶች ስላስተማሩት ትምህርቱ ስህተት ነው ለማለት ሳይሆን፣ ትምህርቱን የሚያስተምሩ ሰዎች እንደልዩ መገለጥ አድረገው ማቅረባቸውና ትምህርቱን የማይቀበሉ ሰዎችን የጌታ መንፈስ እንደጎደላቸው አድርገው ማሰባቸው ትክክል እንዳልሆነ ለትምህርቱ አዳዲስ መምህራንና ደቀመዛሙርት ለማሳየት ነው።

እግዚአብሔር ይባርካችሁ!


  1. በእኔ እምነት “ሰው የሚታይና የሚዳሰስ ውጭዊ ሰውነት እንዲሁም የማይታይና የማይዳሰስ ውስጣዊ ሰውነት ድምር ነው” የሚለው አባባል የተሻለ ነው። ነፍስና መንፈስ የሚባል ሁለት ውስጣዊ ሰውነቶች አሉን ከሚለው ይልቅ እንደ አውዱ አንዳንዴ “ነፍስ” ሌላ ጊዜ “መንፈስ” ተብሎ የሚጠራ አንድ ውስጣዊ ሰውነት አለን ማለትን እመርጣለሁ። አሁን ያለን ውጫዊ ሰውነት የተዋረደ ቢሆንም በዘላለማዊና በከበረ ሰማያዊ አካል እንዲተካልን እንጂ አካልን ጥለን መንፈስ ብቻ መሆንን እንድንናፍቅ መጽሃፍ ቅዱስ አያስተምረንም። ጃፒ “ስጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግስት ሊወርሱ አይችሉም” የሚለውን ደጋግሞ እንደመፈክር መጠቀሙ ግራ የሚያጋባ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። 1ኛ ቆሮ 15 በደንብ ከተነበበ መንፈስም ያለ “ክቡር ስጋ” (ፊል 3፥21) የእግዚአብሔርን መንግስት ሊወርስ አይችልም።
  2. ሐሥ 18፥15
  3. በነገራችን ላይ የዕብራስይጥም ይሁን የግሪክ ቋንቋ እውቀት የለኝም፣ ነገር ግን እድሜ ለቴክኖሎጂ የእያንዳንዱን የእንግሊዝኛ መጽሃፍ ቅዱስ ቃል ከኦሪጂናሉ የዕብራይስጥ ወይም የግሪክ ቃል ጋር የሚያዛምዱና ለቃላቱ ሰፊ ትንታኔ የሚሰጡ ብዙ ሶፍትዌሮችና ድረ-ገፆች አሉ። እነዚህን የመጽሃፍ ቅዱስ ጥናት መርጃ መሳሪያዎች በመጠቀም ኦሪጂናል ቋንቋዎችን ተመስርቼ የሰጠኋቸውን የመከራከሪያ ነጥቦች ትክክለኝነት መመርመር ይቻላል።
  4. በእርግጥ ጳውሎስን ጨምሮ ሌሎች የአዲስ ኪዳን ጸሃፊዎች በአብዛኛው የዕብራስይጡን ሳይሆን የሰብዓ ሊቃናት ተብሎ የሚጠራውን የብሉይ ኪዳን የግሪክ ትርጉም ይጠቀሙ ነበር።
  5. ዘፍ 6፥12፣ ዘዳ 5፥26፣ ኢዮብ 34፥15፣ ኢሳ 40፥6፣ 66፥16፣ 66፥23፣ 66፥24፣ ኤር 12፥12፣ 25፥31፣ 32፥27፣ 45፥5፣ ሕዝ 20፥48፣ 21፥4፣ ኢዮኤል 2፥28፣ ዘካ 2፥13፣ ማቴ 24፥22፣ ማር 13፥20፣ ሉቃ 3፥6፣ ሮሜ 3፥20፣ ገላ 2፥16
  6. ሲኖኒመስ ፓራለሊዝም (Synonymous Parallelism) – አንድን ሃሳብ በተለያዩ ቃላት መደጋገም አጽንኦትን መስጠት ማለት ሲሆን በመጽሃፍ ቅዱስ በስፋት ጥቅም ላይ የዋለ ዘዴ ነው። http://www.oxfordreference.com/view/10.1093/oi/authority.20110803100547720 መመልከት ይቻላል።
  7. “ሰውየው ዳነም አልዳነም ስፒሪት ቢንግ ነው።”
  8. http://www.scientology.org/faq/scientology-beliefs/is-man-a-spirit.html. IS MAN A SPIRIT?
  9. https://www.lds.org/scriptures/gs/spirit. Guide to the Scriptures, Spirit.

10 thoughts on “ሰው መንፈስ ነው? መጽሐፍ ምን ይላል?

  1. ወንድም ኢዮብ
    በጣም የሚያንፅና የሚያነጋግር ፅሁፍ ነው ጌታ ይባርክህ ። ከ ክርክርና የኔ አሳብ ልክ ነው ብሎ ከመሞገት ይልቅ በ እግዚአብሔር ቃል የተፈጠሩትን ትርጉሞች አንተ ካየህበት አንፃር ብቻ ማቅረብህን ወድጀዋለሁ። ሰው መንፈስ ነው የሚለው ትምህርት ሰውን ወደ ትህትና እና እግዚአብሔርን ወደ መፍራት ከወሰደው ችግር የለበትም ሆኖም ከትምህርቱ ጋር የተያያዙ ሰውን በዚህች ምድር ብቻ እግዚአብሔርን ተስፋ እንዲያደርግ አድርጎታል ያ ደግሞ ምስኪንነት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳለው “በዚች ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረግን ከሆነ፥ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን።” (1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 15:19) ትምህርትን መለካት ያለብን ምን ያህል ወደ እግዚአብሔር አቅርቦናል፣ ስጋችን ወይንስ መንፈሳችንን አጠንክሮታል ፣ ምን ያህል ህይወት ሆኖናል የሚል መሆን አለበት። እግዚአብሔርን ለመምሰል የማያስጠጋ ትምህርት ከጌታ አይደለም ። የሚገርምህ በዶክትሪን እንከን የሌለባቸው የሚባሉ አብያተ ክርስቲያናትም ምእምናንን ክርስቶስን ወደ መምሰል የማያስጠጋ ትምህርት ካላስተማሩ ለራሳቸውና ለመንጋው ምሳሌነት ያለው ህይወት ካልኖሩ፣ በእግዚአብሔር መንፈስ ተመርተው ካልመሩ ዶክትሪናቸውን አያድናቸውም። እግዚአብሔር ከዶክትሪን በላይ የሚገደው ህይወት ነው። የህይወት ለውጥ!
    ወደ ተነሳንበት ሐሳብ ልምጣ። አንተ እንዳስቀመጥከው ሰው በእግዚአብሔር አምሳል መፈጠሩ ፣ እግዚአብሔር መንፈስ ስለሆነ ሰውም መንፈስ ነው፣ መንፈስ ደግሞ አንድ ነው ስለዚህ ሰው እግዚአብሔር ነው ወደሚል ትርጉም ይህ ማለት ደግሞ ሳይታሰብ የሰውን ልብ ወደ ዙፋን ይወስደዋል፣ ያ ደግሞ አደገኛ ነው። ለዚያ ነው ይችን ምድር ገዢና አስተዳዳሪ ነን በማለት ሰውን ምድር ጋ ብቻ እንዲጣበቅ የሚያደርገው። በዚህ ትምህርት ላሉ የስኬት ትርጉሙ ሰማይ ሳይሆን ምድር የሚሆነው።
    መፅሐፍ ቅዱስ የሰው ማንነትን እንዲህ ብሎ አስቀምጦታል

    ” የሰላምም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁም ነፍሳችሁም ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ።”
    (1ኛ ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች 5:23)
    ሰው መንፈስ አለው፣ ነፍስ አለው በስጋ ይኖራል። ከ ውድቀት በፊት ሰው ሲፈጠር መንፈስ ተሰጠው እንጂ መንፈስ ሆኖ አልተፈጠረም። እንደዛማ ባይሆን በእግዚአብሔር ፍፁም ማንነት(ስብእና) ሰው መንፈስ ከሆነ አይወድቅም ነበር( መንፈሱ አይሞትም ነበር) በሌላ አነጋገር የሰው እጣ የእግዚአብሔር እጣ ነው እያልን ነው። ሰው ግን መንፈስ አለው ይህ የሚያሳየን ከእግዚአብሔር የተቀበልነው የተሰጠን መሆኑን ነው። ተሰሎንቄ ላይ ጳውሎስ “መንፈሳችሁ” ነፍሳችሁ” ስጋችሁ” ብሎ ሶስት ክፍሎቻችን የነገረን የ “አለን” እንጂ የሆንነው አይደለም። ከውድቀት በሁዋላ የሞተው መንፈሳችን በክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ ባመንን ጊዜ ህያው ሆነ። አሁን ህያው የሆነ መንፈስ አለን በዚህ መንፈስ ውስጥ ደግሞ የእግዚአብሔር መንፈስ ይኖራል።
    ” ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመንፈስህ ጋር ይሁን። ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን፤ አሜን። (2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 4:22)
    ሌላ ጊዜ እጨምራለሁ ለዛሬ እዚህ ይብቃኝ።

    Liked by 1 person

  2. ከላይ ያለውን ሐሳብ ከፃፍኩ በሁዋላ አንድ ሐሳብ ወደ ውስጤ መጣ። ሰው መንፈስ አለው ወይስ ሰው መንፈስ ነው የሚለውን አባባል በበለጠ ያበራዋል ብየ አሰብኩ። አንድ ሰው መኪና አለው ማለት መኪናውን ይጠቀምበታል ወይንም በመኪናው ይታገዛል እንጂ ሰውየው መኪና ነው ማለት አይደለም በጭራሽ ሰው መኪና አይሆንም። አሁንም ስው መንፈስ አለው፣ በመንፈስ ይመራል፣ በመንፈስ እግዚአብሔርን ያመልካል፣ በመንፈሱ ከእግዚአብሔር ጋር ህብረት ያደርጋል እንጂ ሰው መንፈስ አይደለም መንፈስም አይሆንም። ሰው ሰው ነው!

    Liked by 1 person

  3. God bless you, i was amazed with your analysis. you deserve acknowledgement. However, I want to indicate you one point that the teaching of spirit, soul, body would lead to being adulterous as they assumed as their body will not be sanctified in this world and they don’t care about their physical body to do what ever sin. I think their doctrine may be associated with “NOSTITIZEM” who were propagated at the time of (1,2,3, JOHN) saying that body could not be sanctified. so i suggest you that you may relate the teaching with “NOSTISITHM” and lead to ‘NUFAKIE’. After all, the teacher of this schools specially Ours, does not understand what they say and ends up where. They don’t refer even commentary…

    Like

    1. Yohannes, thank you for reading and commenting on it. What I tried to do here is to evaluate whether “man is spirit” teaching is a biblical teaching as it’s currently taught by Japi and a few other contemporary ministers. As you said, the teaching COULD lead to heretical teachings and practices but not necessarily. We should address such heresies when and if they come up, but arguing that some teaching is a heresy not because it’s by itself a heresy but because it COULD lead to a heresy is not something I would prefer to do nor I think it’s a fair and effective argument.

      Liked by 1 person

  4. ስለ ትምህርቱ የሰጠሄው ማብራሪያ እጅግ በጣም አስተምርኛልም አነሳስቶኛልም በጌታችን ስም ተባረክ። ብዙ ከእውነተኛው ወንግል መስመር የሳቱ አስተምሮዎችን መቋቋም(challenge) ማድረግ የምንችልበትን ፀጋና ጥበብ ለሁላችንም ይስጠን አሜን።

    Liked by 1 person

  5. በጣም ጠቃሚና ትውልድን ከጥፋት የሚመልስ መልዕክት ነው። በሌሎቹም የስህተት አስተምህሮዎች ላይ እንደዚህ አይነት ግልጽ እና መጽሀፍ ቅዱሳዊ መልዕክቶችን ብታቀርብልን ጥሩ ነወ።

    Liked by 1 person

  6. የፅሁፉን ማብራሪያ በሚገባ አንብቤ ምን ለማለት እንደተፈለገና ለማስተላለፍ የተፈለገውን ሃሳብ በሚገባ ተመልክቸዋለው እናም ዝርዝር ሃሳቡ እጅግ ጠቃሚና ሚዛን የተጠበቀ የመፅሀፍ ቅዱስ መሰረት ያለው ማባራሪያ ጭምር መሆኑ የፀሃፊውን ብስለትና ትኩረት አጥርቶ የሚያሳይ ነው በዚህ ላይ ለፀሃፊያችን እንደ ተጨማሪ ግብዓትና አስተያየት እንዲሆን ጥቂት ለማለት ወደድኩ፡፡የዚህን ፅሁፍ ዋና ሐሳብ በጥልቀት እንድናየውና በተለይም የፅሁፉ ዝርዝር ሃሳብ ያጠነጠነበት አውድ “ሰው መንፈስ ነው? መጽሐፍ ምን ይላል?”ወይንም “ሰው መንፈስ ነፍስ ስጋ ነው? ” ከሚለው በዘለለ ይህንን አስተምሮ ከክርስቶስ አንፃር ብናየው ምናልባትም ከላይ ከተዘረዘረው ሃሳብ በበለጠ የዚህኛው አስተምሮ ተዛማችንነት ይበልጡን እንድንረዳው ያጓጓናል ብዬ አስባለው ፡፡ምክንያቱም የዓለምን ሐጢያት ለማስወገድ የመጣው ኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ብቻ ነው ካልን ሊያድነን የመጣው ጌታ ፍፁም ሰው ፍፁምም አምላክ መሆኑ ላይ ብዥታ ውስጥ ይከተናል ማለት ነው ፡፡ እናም ከዚህ ጋር በተያያዘ ተጨማሪ ማብራሪያ ቢሰጥበት ለማለት ፈልጌ ነው ይህን ለማለት የወደድኩት ፡፡ በፀሁፉ ማብራሪያና የፅሐፍ ቅዱሳዊ መሰረት ያላቸው ትንታኔ እጅግ ተባርኬባቸዋለው፡፡ ለብዙዎች ብርሃን የሚሰጥ ነው ፡፡

    Liked by 1 person

    1. ኤፍሬም፣ ስለ ገንቢ አስተያየትህ አመሰግናለሁ። ትምህርቱ በነገረ ክርስቶስ ላይ ሊያመጣ የሚችለውን ተጽዕኖ በጥልቀት አላሰብኩበትም። ይህን ትምህርት የሚያስተምሩ ሰዎች ብዙ ጊዜ ለመጽሃፍ ቅዱስ ያላቸው ቦታ ከፍ ያለ ስለሆነ “ክርስቶስ በስጋ እንደመጣ የማይታመን” የሚለውን ጥቅስ የሚያውቁና የሚያከብሩ ስለሆኑ ከዚያ ዓይነት ጥቅስ ጋር በቀጥታ ሊያላትማቸው ከሚችል አስትምህሮ ራሳቸውን እንደሚቆጠቡ አስባለሁ። እንደ አጠቃላይ፣ በየቤተክርስቲያኑ የሚሰጡ ብዙ አስተምሮዎች ከሌሎች መሰረታዊ አስተምሮዎች ጋር ያለቸው ዝምድና ሲስተማቲካሊ የታሰበባቸው አይደሉም። ያ መሆኑ ባንድ በኩል ጥሩ ነው በሌላ በኩል ግን አይደለም። በአንድ አስተምህሮ ላይ የተፈጠረ ችግር ወደ ሌሎች አስተምሮዎች ሁሉ እንዳይዛመት ይረዳል። በሌላ በኩል ግን እርስ በርሱ በደንብ ያልተዋቀረና ያልተናበበ ትምህርትን እንድንከተል ያደርገናል። ወጥነትን ለማስጠበቅ የሚጥሩ ሰዎች ደግሞ ካገኙት ሁሉንም ትምህርታቸውን ሊያስከልሳቸው ብሎም መሰረታዊ አስተምህሮዎች ላይ ስተት ውስጥ ሊከታቸው ይችላል። ይህን አጠቃላይ ችግር ብዙም እንደ የ”ሰው መንፈስ ነው” አስተምህሮ ብቻ ችግር ሆኖ አላየውም። አንዳንዴ ወደ “እንደዚህ አይነት አስተምህሮ ሊወስድ ይችላል” ብሎ ማስጠንቀቂያ ከመስጠት የዘለለ ሚና ኖሮት መካረር ውስጥ ማስገባት የለበትም። ወደዛ አይነት አስተምህሮ ሊከት ቢችልም እስካልከተተ ድረስ ከመካረር ራስን መጠበቁ የተሻለ ነው ብየ አስባለሁ። ግን ያው በነገሩ በጥልቀት ገና ስላላሰብኩበት አጉል መተማመን ሊሆን ይችላል።

      Like

  7. አዮባ ስለ ፃፍከው መፅሐፍ ቅዱሳዊ አተረጓገምን መሠረት ያደረገ እና ሚዛኑን የጠበቀ ማብራሪያ ተባረክ: በኒቆድሞስ ና በኢየሱስ መካከል ያለውን ንግግር ወስደህ ዳግም የተወለደዉ መንፈሳችን እንደሆነ ፅፈሃል:: ዳግም መወለድ ግን መንፈሳችን ከመንፈስ መወለድ ነው ወይስ የሁለንተናችን ከመንፈስ ቅዱስ መወለድ መታደስ …አይደለምን? እንደ ስጋ የተወለደ ና እንደ መንፈስ የተወለደ የሚለው ሀሳብ ከ ገላ 4:29_30 አንፃር እንዴት ይታያል?

    Like

Leave a comment