በ ፕሮቴስታንት (”ጴንጤ”) እና በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነቶች መካከል እንደዋና ልዩነት ከሚታዩት አንዱ አማላጅ ማነው ለሚለው ጥያቄ የሚሰጠው ምላሽ ነው። ፕሮቴስታንቶች ክርስቶስ ነው ሲሉ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ደግሞ ቅድስት ማርያም ናት ይላሉ፣ አያይዘውም እንዴት አምላክ ራሱ ተማላጅ ደግሞም አማላጅ ይሆናል ይላሉ። ይህ ሁሌም የሚያወዛግብ ሁሉም የሚያውቀው ልዩነታችን ይሁን እንጂ በአማላጅነት ዙሪያ የፕሮቴስታንቱ አመለካከት በእርግጥ ምን ይመስላል የሚለውን በሰከነ መልኩ ለመስማትና ለመገምገም እድሉን ያላገኘ በጣም ብዙ ሰው እንዳለ አስባለሁ። እኔም የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ እንደመሆኔ ስለ አማላጅነት በፕሮቴስታንቱ ዘንድ ያለውን አመለካከት በዚህ አጭር ጽሁፍ ለማቅረብ እሞክራለሁ። በዚህ ጽሁፍ የቀረበው አመለካከት ከሞላ ጎደል የብዙሃኑን የፕሮቴስታንት ቤተ እምነቶች አቋም የሚያንጸባርቅ እንደሆነ ባምንም ከቤተ እምነት ቤተ እምነት ከግለሰብ ግለሰብ ጥቂት የማይባል የትምህርትና የአመልካከት ልዩነት በዚህ ዙሪያ ስለሚኖር አንባቢው ይህን በመገንዘብ ጽሁፉን እንደ አንድ ግለሰብ ጽሁፍ እንጂ በቤተ እምነቶች እንደተሰጠ የአቋም/የእምነት መግለጫ አድርጎ እንዳይወስደው ማሳሰብ እወዳለሁ። ለማንበብ በሚያሰለች መልኩ ጽሁፉ እንዳይራዘም ስል የተጠቀምኳቸውን የመጽሃፍ ቅዱስ ጥቅሶች ሙሉ በሙሉ ለመጻፍም ይሁን ለማብራራት አልቻልኩም። በማብራራት የሚባክነውን ቦታ ለመቀነስ ስል በትዕምርተ ጥቅስ ውስጥ ያሉት ጥቅሶች ላይ ባጭሩ ለማብራራት ይጠቅማሉ ብየ ያሰብኳቸውን የራሴን ቃላት በካሬ ቅንፍ ([]) ውስጥ አስቅምጫለሁ።  ከጽሁፉ ጎን ለጎን መጽሃፍ ቅዱስን ከፍቶ የቀረቡትን ሁሉንም ጥቅሶች ትኩረት ሰጥቶ አንባቢው እንዲያነባቸው አደራ እላለሁ።

የተነሳንበትን ጥያቄ ለመመለስ እንዲረዳን ከቃሉ እንጀምር። ማማለድ የሚለው ቃል በመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ ከዋለበት አጠቃቀም አንጻር ሁለት ዋና ትርጉሞች እንዳሉት ለማሳየት እሞክራለሁ፦

የመጀመርያው ትርጉም፦ ለሌላ ሰው መጸለይ ማለት ነው። ለዚህ እንደማስረጃ የሚሆነው፦ 1ኛ ጢሞቲዎስ 2፥1፦ “እንግዲህ እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር፥ ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ።” ይህ ምልጃ (የምልጃ ጸሎት) ማንኛውም አማኝ ሊያደርገው የተሰጠ መብትም ሀላፊነትም ነው ብለን ከጥቅሱ መገንዘብ እንችላለን። ለዚህ አይነቱ አገልግሎት ብዙ ምሳሌዎችን ከመጽሃፍ ቅዱስ ማየት እንችላለን፦ አብርሃም ለሰዶም ከተማ የጸለየው (ዘፍ 18፥23-33)፤ ይስሃቅ ለአቤሜሌክ የጸለየው (ዘፍ 20፥7)፤ ኢዮብ ለጓደኞቹ (ኢዮብ 42፥8) የጸለየው፤ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ለበሽተኛው እና አማኞች እርስ በርሳቸው ( ያዕቆብ 5፥15-16) የሚጸልዩት፣ እስጢፋኖስ ለወጋሪዎቹ (ሐዋ 7፥60) እንዲሁም ተራው አማኝ ለመሪዎቹ (ቆላ 4፥3፣4) የሚጸልዩትን ያጠቅላል፣ እነዚህ ሁሉ ግን በምድር በህይወት ለነበሩና ስለነበሩ አማኞች የተጻፉ መሆናቸውን እንዲሁም “ታላላቅ” ቅዱሳን ለ “ታናናሽ” ቅዱሳን ብቻ ሳይሆን ተራው ምዕመን ጳውሎስን ለመሰለ ሐዋሪያ የምልጃ ጸሎት እንዲያቀርብ ሐዋሪያው ጳውሎስ ራሱ መጠየቁን ልብ እንበል። ይህ አይነቱ ምልጃ ለተወሰኑ አማኞች (ጻድቃን) ብቻ የተሰጠ ካለመሆኑ በተጨማሪ ምድር ላይ በህይወት ያሉ ሰዎች ላይ ያተኮረ ነው። ከክፍሎቹ እንደምንረዳው የምልጃ ጸሎት ሰዎችን እግዚአብሔር ይቅር እንዲላቸው ወይም ከበሽታ እንዲፈውሳቸው ወይም ስኬት እንዲሰጣቸውና የመሳሰሉትን ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ቀጥሎ ባለው አንቀጽ የምልጃ ጸሎት የሰውን ሃጢያት ለማስተሰረይ ወይም ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር ለማስታረቅ በራሱ ብቃት ያለውና የግድ አስፈላጊም እንዳልሆነ ለማሳየት እሞክራለሁ። የምልጃ ጸሎት  ውጤትም እንደማንኛውም ጸሎት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድና እንደሚጸለይለት ሰው የልብ ሁኔታ የሚወሰን ይሆናል። ለምሳሌ አንድ አማኝ ወይም ጻድቅ  ለአንድ ሰው እግዚአብሄር ሃጢያቱን ይቅር እንዲለው ቢጸልይና የተጸለየለት ሰው ግን ንስሃ በእግዚአብሔር ፊት ለመግባት ፈቃደኛ ባይሆን ስለጸለየው ጻድቅ ወይም ስለተጸለየው ጸሎት ሲል እግዚአብሔር የሰውየውን ሃጢያት ያለ ንስሃ እንዲሁ ይቅር ሊለው አይችልም።  ወይም አንድ አማኝ ወይም ጻድቅ – ለአንድ ሰው መፈወስ ቢጸልይና የእግዚአብሔር ፈቃድ ግን ባይሆን፣ ያ ሰው አይፈወስም። እንግዲህ እንዲህ ባለው የማማለድ አገልግሎት ውስጥ ቅድስት ማርያም ብቻ ሳትሆን ሁሉም እውነተኛ አማኝ ሊሳተፍበት ይችላል ይገባልም።

ሁለተኛው ትርጉም፦ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ሆኖ ማስታረቅ ወይም የማስታረቅ ስራ መስራት ማለት ነው። ይህኛው የማስታረቅ ወይም የማማለድ አገልግሎት እንደመጀመሪያው በጸሎት ወይም በቃላት ልመና የሚደረግ አይደለም። ይህን ለማብራራት እንዲረዳኝ ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ ልስጥ፦ à የተጣላው ማነው? ሰውና እግዚአብሔር à የተጣሉበትስ ምክንያት? ሃጢያት (ኤፌሶን 2፥1-3፣ ሮሜ 3፥23) à ለእርቃቸው የተቀመጠው ቅድመ ሁኔታ ምንድን ነው? – የጥሉ ምክንያት የሆነውን የሰው ሃጢያት መደምሰስ ወይም ይቅር ማለት à ታዲያ እግዚአብሔር ሃጢያትን ለምን እንዲሁ ይቅር አይልምና አይታረቁም? – እግዚአብሔር የፍትህ አምላክ ስለሆነ በምሳሌ 11፥21 እንዲህ ይላል “ክፉ ሰው እጅ በእጅ ሳይቀጣ አይቀርም “፤ እንዲሁም ዘጸአት 32፥33-35 እና ዘጸአት 34፥7ን ስናነብ እግዚአብሔር እንዲሁ “በደለኛውንም ከቶ እንደማያነጻ [ሳይቀጣ እንደማይቀር]” በግልጽ እናያለን። ከቀጣው በኋላ እርቅ ይወርዳል እንዳንል ደግሞ “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና” (ሮሜ 6፥23) ሰው እርቅ ላይ ሳይደርስ መሞቱ ነው።

እግዚአብሔር የሰዎችን ሃጢያት ይቅር ለማለት በሰዎች ሞት ፋንታ እንስሳት እንዲሰው በብሉይ ኪዳን እንዴት እንዳዘዘ ማየቱ እግዚያብሔር ለእርቅ ብቻ ሳይሆን ለፍትሃዊነትም ያለውን ቦታ እንድንረዳ ያግዘናል። እግዚአብሔር እስራኤላዊያንን ይቅር ማለት ይወዳል ግን ደግሞ ሐጢያታቸው ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝም ይፈልጋል። ለዚህም ነው የሙሴን ሕግ በመከተል ለሃጢያታቸው ስርየት እንስሳትን ይሰው የነበረው። የዕብራዊያን ጸሃፊ በምዕራፍ 9 ቁጥር 22 ላይ “ደምም ሳይፈስ ስርየት የለም” በማለት ለሃጢያት ስርየት ስርየቱንም ተከትሎ ለሚመጣው እርቅ የደም መፍሰስን አስፈላጊነት በማያወላዳ መልኩ ያስቀምጠዋል። በዚህ ሁለተኛው የማማለድ ትርጉም መሰረት የማማለድ ስራው ሰውና እግዚአብሔርን ማስታረቅ ሲሆን የሚታረቁት ደግሞ የጥላቸው መሰረት የሆነው ሃጢያት ሲዎገድ ብቻ እንደሆነ አይተናል፤ ሃጢያት ደግሞ ደም ሳይፈስ በልመና (በምልጃ ጸሎት) እንደማይወገድ ተመልክተናል። ስለዚህ ይህን ጉዳይ በሰውና በእግዚአብሄር መካከል ሆኖ ለመፈጸም ብቃት ያለውና የፈጸመው ማነው ብለን ስንጠይቅ፣ 1ኛ ጢሞ 2፥5-6 እንዲህ በማለት ምላሽ ይሰጠናል፦ “አንድ እግዚአብሔር አለና፥ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ ራሱንም ለሁሉ ቤዛ ሰጠ”። መካከለኛው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው ካለን በኋላ ክርስቶስን መካከለኛ ያስባለው ምኑ እንደሆነ ደግሞ “ራሱንም ለሁሉ ቤዛ ሰጠ” በማለት መካከለኛነቱ ለሃጢያት ማስተሰረያ የሚሆነውን ሞት በመሞቱና ደም በማፍሰሱ ምክንያት እንደሆነ ያስረዳናል። እንዲሁም በሌላ ስፍራ ጌታ ኢየሱስ እንዴት አድርጎ እንዳስታረቀን ደግሞም እንደሚያስታርቀን ሲያስረዳን ሮሜ 5፥10 እንዲህ ይላል “ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ታረቅን” እንዲሁም በሮሜ 3፥25 “እርሱንም [ኢየሱስን] እግዚአብሔር በእምነት የሚገኝ በደሙም የሆነ ማስተስሪያ አድርጎ አቆመው” በማለት የምንታረቀው በጌታ ሞት ወይም በደሙ እንጅ በአንደበት ልመናው (በምልጃ ጸሎቱ) እንዳልሆነ ያስገነዝበናል። ለዚህ ነው ጌታ ኢየሱስ በሮሜ 8፥34 “ስለኛ የሚማልደው” የተባለው (በዚህ ዙሪያ ስላለው ውዝግብ ከታች በጥያቄ ቁጥር 1 ላይ አጠር ያለ መልስ ሰጥቻለሁ)። እዚህ ላይ ማስታወስ ያለብን የሚማልደው ስንል ተንበርክኮ የሚለምነው ማለት አይደለም፣ እሱኛው አገልግሎት በምድር ላይ ያሉ አማኞች ለሌሎች አማኞች ወይም ሰዎች የሚጸልዩት ጸሎት እንደሆነ አይተናል። ይህኛው (ሁለተኛው) የማማለድ አገልግሎት ግን ሰዎችን ከሃጢያታቸው በማንጻት ከእግዚአብሄር ጋር የማስታረቅን ወይም ወደ እግዚአብሄር የማቅረብን ስራ የሚመለከት ነው (ኤፌ 2፥13-18)። ይህ ጌታ ኢየሱስ ብቻ ይሰራዋል ያልነው የምልጃ አይነት መጀመሪያ ከጠቀስኩት የምልጃ አይነት በውጤቱም ቢሆን እንደሚለይ ደግሞ ዕብ 7፥24-25 “እርሱ [ክርስቶስ] ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል።” በማለት በኢየሱስ የማማለድ ስራ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡ ሰዎች እርግጠኝነት እንደሚድኑ ያሳየናል። “ዘወትር በህይወት ይኖራል” የሚለው ቃልም የኢየሱስ የምልጃ ስራ ምድር ላይ በነበረው ቆይታ ብቻ የተገደበ እንዳልሆነ ያሳያል። የሞተውና ደሙን ያፈሰሰው ምድር ላይ በነበረ ጊዜ የዛሬ 2000 ዓመታት ገደማ ይሁን እንጂ ያ ሞቱና ደሙ ግን እርሱ ሲሞት በህይወት ለነበሩ ሰዎች ብቻ የተገደበ አይደለም። ይልቁንም ኢየሱስ “ስለ ብዙዎች ለሃጢያት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው” እንዳለ በየትኛውም ጊዜና ቦታ ይሁኑ በአዲስ ኪድን ዘመን ላሉ ሁሉ አማኞች ለሃጢያት ይቅርታ የሚሆን ብቸኛው የምልጃ ስራ ነው። ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ ያማለዳል ሲባል በአሁን ሁኔታው በአባቱ ቀኝ ሆኖ የምልጃ ጸሎት ያቀርባል ማለት ሳይሆን ስለኛ ሃጢያት ብሎ ባፈሰሰው ደም ከማንኛውም ሃጢያት አንጽቶ ከእግዚአብሄር ጋር ታርቀን ህብረት እንዲኖረን ያደርጋል ወይም ከላይ ባየነው የዕብራዊያን ጥቅስ መሰረት “ያድነናል” ማለት ነው። ያልዳነ ከእግዚአብሔር ጋር ህብረት ሊኖረው አይችልምና፣ ወደ እግዚአብሔርም የምንመጣው ወይም የምንቀርበው ስለዳንን እንጂ ለመዳን አይደለም፣ ሃጢያታችንም ከተወገደ በኋላ እንጂ ለማስወገድ አይደለም። ለዚህም ነው ኢየሱስ “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።” (ዩሃ 14፥6) ያለው። ወደ አብ የምንመጣው መንገድ የሆነውን ኢየሱስን አግኝተን እውነት የሆነውን እርሱን አውቀንና ህይወትንም አግኝተን ጨርሰን እንጂ ገና ለማወቅና ለማግኘት አይደለም። ይህንም የምለው ወደ አብ መቅረብ ምን ያህል ከምልጃ ጸሎት ያለፈ ቅድመ ሁኔታ እንዳለው ለማሳየትና ይህንንም ሁሉ ቅድመ ሁኔታ አሟልቶ ወደ እግዚአብሔር ለማቅረብ የሚቻለው ለሃጢያታችን ስርየት በመሞት መንገድም እውነትም ህይወትም ለሆነው ለጌታ ኢየሱስ ብቻ መሆኑን ለማስገንዘብ ነው። ኢየሱስ አማላጅ ነው ሲባልም ከሃጢያታችን አንጽቶና ከሞት ፍርድ አድኖ ሌሎች ቅዱሳን ወዳሉበት የአብና ወልድ ህብረት የሚቀላቅለን አዳኛችን ነው ማለት ነው (1ኛ ዩሃ 1፥3)። ቅድስት ማርያም አታማልድም ሲባል ለሌሎች ሰዎች የምልጃ ጸሎት አትጸልይም ነበር ለማለት ሳይሆን፣ ለሰው ልጆች ሃጢያት ስረየት ብላ ስላልሞተችና ልትሞትም ስለማትችል በእርሷ በኩል ሃጢያታችን ይቅር ተብሎ ከእግዚአብሄር ጋር ልንታረቅ አንችልም ማለታችን ነው። በእርሷም ይሁን በሌላ ሰው ጸሎት ምክንያት ደግሞ የሃጥያት ይቅርታ ብሎም ከእግዚአብሔር ጋር እርቅ የማናገኝ ከሆነ አማላጅ የሚለው ቃል ለቅድስት ማርያምም ይሁን ለሌላ ሰው ጥቅም ላይ ሊውል አይችልም ማለት ነው። ለዚህም ነው በአዲስ ኪዳን ከኢየሱስ ሌላ አማላጅ የሚለው ቃል ለማንም ሰው ይሁን መልአክ ጥቅም ላይ ያልዋለው። መካከለኛው ክርስቶስ እንጂ ሌላ አይደለምና። በሰውና ሰው በሆነው በኢየሱስ ደግሞ መካከልኛ የለም አያስፈልግምም (1ኛ ጢሞ 2፥5)። ከላይ እንዳየነው አማላጅ ማለት አዳኝ ነውና ኢየሱስ አዳኝ ወይስ አማላጅ የሚለው ጥያቄ በአዲስ ኪዳን ያለውን የአማላጅነትንም ይሁን የአዳኝነትን አጠቃቀም ግንዛቤ ውስጥ ያላስገባ ጥያቄ ነው ብለን ልንደመድም እንችላለን። ሳያድነን ሊያማልደን (ሊያስታርቀን) አይችልምና ስለሃጢያታችን ይቅርታ ደሙን በማፍሰሱና በመሞቱ ከሐጢያትና ከሞት በማዳን ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቀናል (ያማልደናል)።

ነገር በምሳሌ

ከዚህ ሁሉ ማብራሪያ በኋላ የአማላጅነትና የአዳኝነት አንድ መሆን ላልተዋጠላቸው አንድ ተጨማሪ አገላለጽ በምሳሌ ልጨምርና ወደ ጥያቄና መልሶች ልግባ። አንድ በመጠጥ ሱስ ምክንያት ከባለቤቱና ከልጆቹ ጋር ሰላም የሌለውን ሰው እንደምሳሌ እንውሰድ። ይህ ሰው አበበ ይባላል ተስፋ የተቆረጠበት በአንድ ጆሮው ሰምቶ በሌላው የሚያፈስ ለመካሪ ያስቸገረ ሰው ነው። አንድ ቀን ግን እሱ ራሱ ከዚህ በፊት በመጠጥ ሱስ የተጠመደ የነበረ ሰው ይተዋወቃል። ከጨዋታ ጨዋታ ስለ መጠጥ ይነሳና ያ ቀድሞ ሱሰኛ የነበረ ሰው በመጠጥ ሱስ ምክንያት ስለደረሰበት የጤና፣ የኢኮኖሚና ማህበረዊ ችግሮች አበበን በስፋት ያጫውተዋል። እንዴት ህይወቱ ኪሳራ ውስጥ እንደገባች፣ ከተከበረ ስራው እንዴት እንደተፈናቀለና ትዳሩ እንዴት መልሶ ሊስተካከል በማይችል ሁኔታ እንደፈረሰ ልብ በሚነካ መልኩ ያወጋለታል። የመጠጥ ሱስን ከዚህ ቀደም በዚህ የክፋት ደረጃው አስቦት የማያውቀው አበበም በሰውየው እጅግ አሳዛኝ የህይወት ታሪክ ነግ በኔ ብሎ በጣም ስለፈራ መጠጥን ከዚያች ቀን ጀምሮ ርግፍ አድርጎ ይተዋል። አበበ ስለዛ ሰው ሲያወራ አንዳንዴ ከመጠጥ ሱስ ያዳነኝ ሰው ነው ይላል፣ አንዳንዴ ደግሞ ከባለቤቴ ጋር በሰላም እንድኖርና ልጆቼን እንዳሳድግ ያደረገኝ ሰው ነው ይላል፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ገንዘቤን ከብክነት ያዳነ በሌሎች ሰካራም ጓደኞቼም ከመብዝበዝ ነጻ ያወጣኝ ሰው ነው ይላል። ሰውየው ለአበበ ያደረገው አንድ ነገር ብቻ ቢሆንም ከተለያየ አቅጣጫ ሲታይ ሰውየው ያደረገው ነገር አንዴ አዳኝ፣ ሌላ ጊዜ ሸምጋይ፣ ደግሞ ሌላ ጊዜ ነጻ አውጭ ሊያስብለው ይችላል። ጌታ ኢየሱስም በመስቀል ላይ አንዴ የሰራው አንዱ ስራው አምነው ለሚከተሉት ከሞት ፍርድ የሚድኑበት ስራው ነውና ከእነርሱ አንጻር ሲታይ አዳኝ ያስብለዋል፣ በሃጢያት ምክንያት ከእግዚአብሔር ተለይተው የነበሩትን ደግሞ ወደ እግዚአብሔር የሚመልስ ስራው ነውና ይኸው ስራው በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ተፈጥሮ ከነበረው ጠላትነት አንጻር ሲታይ አስታራቂ ወይም አማላጅ ያስብለዋል (ኤፌ 2፥16-18)፣ በባርነት ከተያዝንበት የሃጥያትና የዲያብሎስ ቀንበር ደግሞ ነጻ የሚያወጣን ይኸው አንዱ የመስቀል ስራው ነውና ከዚያ አንጻር ሲታይ ነጻ አውጭ ያስብለዋል (ገላ 5፥1፤ ቆላ 1፥13)፣ ደግሞም ይኸው ስራው በአይሁድና በአህዛብ መካከል የነበረውን ልዩነት ያጠፋ ስለሆነ በአይሁድና በአህዛብ መካከል ከነበረው ግንኙነት አንጻር ሲታይ አዋሃጅ ያስብለዋል (ኤፌ 2፥14-15)። አዳኝነቱ ወይም ነጻ አውጭነቱ ወይም አዋሃጅነቱ በጊዜና በቦታ ያልተገደበ ዛሬም የሚሰራ እንደሆነ ሁሉ አስታራቂነቱም (አማላጅነቱም) ዛሬም የሚሰራና በተወሰኑ ጊዜያት ወይም የሃጥያት አይነቶች ብቻ ያልተገደበ ነው። አበበ ከመጠጥ ሱሱ ሳይድን በትዳሩ ሰላም ሊወርድና ገንዘቡን ከሚያጫርሱት የመጠጥ ጓደኞቹም ነጻ ሊወጣ አይችልም ነበር። ከሚስቱ ጋር ላገኘው እርቅና ከበዝባዦቹ ነጻ ለመውጣቱ መሰረት የሆነው ከሱስ መትረፉ ነው። እኛም ከእግዚአብሔር ጋር ለምናገኘው እርቅና ከዲያብሎስ ቀንበር ነጻ ለመውጣታችን ብቸኛው መሰረት በክርስቶስ ደም ነጽተን መዳናችን ነው። ይህም መሰረት (የምልጃ ስራ) በቅድስት ማርያም ወይም በህይወት ባለ ሌላ ጻድቅ ወይም በመልአክ ጸሎት ሊተካ የማይችል ብቸኛ የክርስቶስ ስራ ነው።

የማብራሪያ ጥያቄዎች

ከላይ ባየናቸው ትርጉሞች መሰረት በብዛት እንደመከራከሪያ ነጥብ የሚነሱ ጉዳዩችንና ጥቅሶችን እስኪ እንመርምራቸው።

  1. በሮሜ 8፥34 “የሚማልደው” የሚለውን “የሚፈርደው” ብሎስ መተርጎም ይቻል የለ እንዴ?

አይቻልም ባይ ነኝ። ምክንያቴም አንደኛ የአማርኛ ቋንቋ ራሱ ስለማይፈቅድልን። አማርኛ ተናጋሪ የሆነ ሁሉ በቀላሉ እንደሚረዳው በ”የሚማልድ”ና “የሚማለድ” (ማ ትጠብቃለች) መካክል ሰፊ ልዩነት አለ፣ የመጀምሪያው አማላጁን ሲያመለክት ሌላኛው ተማላጁን ያሳያል። ሁለተኛ የሮሜ 8፥34 አውድ ራሱ “የሚፈርደው” ብሎ ለመተርጎም ፈጽሞ አይመችም። ከክፍሉ አውድ ማየት እንደሚቻለው የክፍሉ ዓላማ “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ስለሆነ ማንም አይቃወመንም፣ ማንም አይከሰንም፣ ማንም አይኮንነንም” የሚለውን ሃሳብ ማስተላለፍ ነው። እንዲሁም የሚኮንነንም የሌለው በአባቱ ቀኝ ሆኖ ስለእኛ የሚማልድልን ክርስቶስ ስለሆነ ነው በማለት ክርስቶስን የመሰለ አማላጅ ስላለን ማንም ሊኮንነን እንደማይችል ማስረገጥ ነው። ይህ ደግሞ ምዕራፉን (ምዕራፍ 8ን) ሲጀምር “በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኩነኔ የለባቸውም” ብሎ ከነገረን ጋር በእጅጉ የሚጣጣም ሃሳብ ነው። “የሚማልደው” የሚለውን ቃል በ“የሚፈርደው” ከቀየርነው ግን አሁን እንዳብራራሁት ከአውዱ ጋር በእጅጉ የተስማማን ትርጉም ልናገኝ አንችልም። ሶስተኛ ከአማርኛ ቋንቋ ውጪ በሁሉም በስፋት በሚነገሩ የዓለም ቋንቋዎች ቃሉ አሻሚ ባልሆነ መልኩ “ይማልዳል” ተብሎ መቀመጡ። አራተኛ አዲስ ኪዳን በተጻፈበት ጥንታዊ የግሪክ ቋንቋ ትርጉሙ በማያሻማ መልኩ “ማማለድ” ሆኖ መቀመጡ ብቻ ሳይሆን አማርኛው በግልጽ ማማለድ ብሎ ከተረጎመው የዕብ 7፥25 የግሪክ ቃል ጋር አንድ አይነት መሆኑ ቃሉን “የሚማልድ” እንጂ “የሚፈርድ” ብለን እንድንተረጉም አይፈቅድልንም። እግረ መንገዴን ማሳሰብ የምፈልገው “ማማለድ” የሚለውን ሃስብ ከምልጃ ጸሎት (ከልመና) ለይተን ማየት እንዳለብን ነው። በአባቱ ቀኝ ሆኖ ስለ እኛ ይማልዳል ማለት በአባቱ ቀኝ ሆኖ ስለ እኛ ይጸልያል ወይም ይለምናል ማለት ሳይሆን አንዴ በፈጸመው የመስቀል ላይ ስራው አሁንም በርሱ በኩል የሚመጡትን (በእርሱ የሚያምኑትን) ከኩነኔ ነጻ ያደርጋቸዋል፣ አብም ከኩነኔ ነጻ ስለሆኑ ልጆቹ ብሎም ወራሾች አድርጎ ይቀበላቸዋል ማለት ነው። ያቀረብኳቸው አራት ምክንያቶች ባያሳምናችሁና “የሚማልደው” የሚለውን “የሚፈርደው” ብሎ መተርጎም ይቻላል ብላችሁ እንኳ ብታስቡ የክርስቶስ አማላጅነት በሮሜ 8፥34 ላይ ብቻ የተንጠለጠለ አስተምህሮ እንዳልሆነ ከላይ በግልጽነት ለማሳየት የቻልኩ ይመስለኛል።

  1. በዩሃንስ ወንጌል 2፥1-9 መሰረት ማርያም የማማለድ ስራ አልሰራችምን?

ማማለድ ስንል በቃና ዘገሊላ ለሰርግ የጠሯትን ጎረቤቶቿን (ዘምዶቿን) ወክላ ለኢየሱስ ጥያቄ (ጸሎት) አቅርባለች፣ ጥያቄዋም ምላሽ አግኝቷል ለማለት ከሆነ መልሴ “አዎን፣ በዚህ ስፍራ ማርያም አማልዳለች” ይሆናል። ይህን ዓይነት የማማለድ ስራም በአንደኛው የማማለድ ትርጉም ስር ሽፋን የሰጠነው ነው። በወንጌል እንዲህ ያለውን የምልጃ ጥያቄ (ጸሎት) ያቀረበች ቅድስት ማርያም ብቻ ሳትሆን አስቀድሜ እንዳልኩ ሌሎችም ሰዎችም አድርገውታል ሊያደርጉትም ይገባል። ለምሳሌ የአይሁድ ሽማግሌዎች የመቶ አለቃውን ወክለው ስለባሪያው (ሉቃ 7፥2-10)፣ ሲሮፊንቃዊቷ ሴት ስለልጇ (ማር 7፥26-30) እንዲሁም ማርያምና ማርታ ስለታመመው ወንድማቸው ስለአልዓዛር (ዩሃ 11፥1-7) ይህንኑ የመሰለ ጥይቄ አቅርበዋል (ጸልየዋል)። ይህ የምልጃ ጥያቄ (ጸሎት) ግን ኢየሱስ ብቻ ከሚሰራው የምልጃ (የማዳን) ስራ ጋር ተነጻጻሪ እንዳልሆነ ምትክም ሊሆን እንደማይችል ከላይ ተመልክተናል።

  1. ቅድስት ማርያም አታማልድም ማለት ክብሯን አያሳንስምን?

የቅድስት ማርያምም ይሁን የሁሉም ቅዱሳን አማኞችና መላእክት አላማ “እርሱ [ክርስቶስ] [እንዲ]ልቅ” (ዩሃ 3፥30) እንጂ ለክርስቶስ ብቻ የተሰጠውን በእግዚአብሔርና በሰው መካከላኛ (አማላጅ) የመሆንን ድርሻ በመጋራት ራሳቸውን ከፍ ከፍ ማድረግ ስላልሆነ ለቅዱሳን ይሁን ለመላእከት ጌታ የፈቀደላቸውን ቦታ ብቻ መስጠት ከቅዱሳንና መላእከት ጋር የሚያወዳጀን እንጂ የሚያጣላን ወይም የማርያም ጠላቶች የሚያስብለን አይደለም። ይህንንም ማድረግ የቅድስት ማርያምን “የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” የሚለውን ምክርን በመጠበቅ እንድናከብራት ያደርገናል እንጂ የእርሷን ክብር ቅንጣት አይቀንሰውም።

  1. ክርስቶስ አማላጅ ነው ማለት ክብሩን አያሳንስምን?

ከላይ እንዳየነው ክርስቶስ አማላጅ ነው ማለት ክርስቶስ መካካለኛስ ነው ማለት ነው፣ ሃጢያትና በደላችንን ደምስሶ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያስታርቀን አዳኛችን ነው ማለት ነው። አዳኝ ክርስቶስ ብቻ ነው ማለት ባፈሰሰው ደሙም ከእግዚአብሔር ጋር የምንታረቅበት ብቸኛው መንገድ ነው ማለት ክብሩን ለሌላ ከማጋራት ይጠብቀናል እንጂ ክብሩን ቅንጣት አይቀንሰውም።

  1. የኢየሱስ ደም (ሞት) የሚያነጻን ካለፈ (ከውርስ) ሃጢያት ብቻ አይደለምን?

በጭራሽ፣ የኢየሱስ ደም ከማንኛውም ሀጢያት በማንኛውም ጊዜ እንደሚያነጻን 1ኛ ዩሃንስ 1፥7 እና 2፥1-3 በግልጽ ያስተምራሉ። የክርስቶስም የምልጃ (የአንደበት ልመና እንዳልሆነ ለማስታወስ እወዳለሁ) አገልግሎት ምድር ላይ ያቆመ ሳይሆን አሁንም ትኩስ በሆነ ደሙ የሰዎችን ሃጢያት እየደመሰሰ ከእግዚአብሔር ጋር እንደሚያስታርቃቸው 1ኛ ዩሃንስ 2፥1-3፣ ዕብ 7፥25 እንዲሁም ዕብ 9፥24-26 በግልጽ ያስተምራሉ።

  1. ኢየሱስ ከማን ጋር ነው የሚያስታርቀን?

ከእግዚአብሔር ጋር! እግዚአብሔር ስንል አብን፣ወልድን፣መንፈስ ቅዱስን ማለታችን ነው። ታዲያ ወልድን ከጨመረ ራሱን በራሱ ይለምናል ማለት ነውን? አይደለም – በሁለተኛው ማለትም ጌታ ኢየሱስ ብቻ በሚሰራው የምልጃ ስራ ማማለድ ማለት በአንደበት መለመን ማለት ሳይሆን ሀጢያትን ይቅር ማስባል የሚችል ደም ማቅረብ እንደሆነ ለማሳየት ሞክሪያለሁ። ስለዚህ አንድ ሰው ወደ ጌታ ኢየሱስ ቀርቦ “ይቅር በለኝ” ሲል፣ ወልድ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ በሚለየው ግብሩ ለሰው ልጆች ሃጢያት ማስተሰረያ የሚሆን ደሙን ስላፈሰሰ ያንን ሰው ሳይኮንነው ይቀበለዋል፤ አብና መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በሮሜ 8፥1 እንደሚናገረው “በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኵነኔ [ስሌለ]ለባቸው” ያንን ሰው ሳይኮንኑ ይቀበሉታል ማለት ነው።

  1. ጻድቃን ስለኛ እንዲጸልዩ (የምልጃ ጸሎት እንዲያቀርቡ) ወደ እነርሱ መጸለይስ እንችላለን?

በጭራሽ፣ መጽሃፍ ቅዱሳዊ አይደለም። ወደየትኛውም ጻድቅ ሰው (በህይወትም ያለ ይሁን የሌለ ወይም የተነጠቀ) መጸለይ ትክክል አለምሆኑን የሚያሳዩ 3 ምክንያቶች ላቅርብ፦ አንደኛ፣ በመጽሃፍ ቅዱስ አንድ ሰው ወደ ሌላ በህይወት ያለም ይሁን የሌለ ሰው ሲጸልይ ፈጽሞ ስለማናይና ይልቁንም በመጽሃፍ ቅዱስ እንደምናየው ጸሎት ሁልጊዜ ወደ እግዚያብሔር ብቻ በመሆኑ። ሁለተኛ፣ ራዕይ 5፥8። 8፥3፡4 የአማኞች ጸሎት በእግዚአብሔር ፊት የሚቀርብ የአምልኮ እጣን እንደሆነ እናያለን። ስለዚህ ጸሎት ራሱ አምልኮ ስለሆነና ከእግዚአብሔር በቀር ማንንም ማምለክ ስለሌለብን ወደ ፍጡር መጸለይ ትክክል አይደለም። ሶስተኛ፣ ወደ ፍጡር መጸለይ የእግዚአብሔርን ባህርይ/ክብር ለፍጡር ማላበስ ስለሆነ። ስለሌሎች ሰወች መጸልይም ይሁን ሌሎች ስለእኛ መጸለያቸው ክርስቲያናዊ መብታችንና ሃላፊነታችን ቢሆንም፣ እንዲጸልዩልን ወደ “ጻድቃን” መጸለይ ግን በሁሉም ወይም በብዙ ቦታ በአንድ ጊዜ እንደ እግዚአብሔር መገኘት ይችላሉ ብለን እንድናስብ፣ የሁሉንም ሰው ቋንቋ እንደ እግዚአብሔር መስማት ይችላሉ ብለን እንድናምን፣ ሰወች በልባቸው ወይም ድምጻቸውን እንኳ ዝቅ አድርገው የሚጸልዩትን ሁሉ ጸሎት እንደ እግዚአብሔር መስማት ይችላሉ ብለን እንድናምን፣ እንዲሁም ርቀት ወይም ሌላ ነገር ሳይገድባቸው እንደ እግዚአብሔር ሲጠሩ ይሰማሉ ይመልሳሉም ብለን እንድናስባቸው በማድረግ የእግዚአብሔርን ክብርና ቦታ እንድንሰጣቸው ያደርገናል። በመጽሃፍ ቅዱስ እንደምናየውና ጳውሎስ እንዳደረገው ሌሎች እንዲጸልዩልን በደብዳቤ ወይም በአካል ወይም በመልክተኛ ወይም በሌሎች ዘመናዊ መንገዶች ተጠቅመን መንገር እንችላለን እኛም ለቤተሰቦቻችን፣ ጓደኞቻችን፣ በቅርብም ይሁን በሩቅ ለምናውቃቸው አማኞችና ሰዎች መጸለይ እንችላለን ይገባናልም። ወደ ፍጡር መጸለይ ግን ፍጡራንን እንደእግዚአብሄር ማየትና ማክበር ነው ስለዚህም ጣኦት አምልኮ ነው ብየ አምናለሁ። ይህ እንግዲህ ለጻድቃን በጸሎት የሚቀርበውን ምስጋናና ውዳሴ ወይም መዝሙር ሳይጨምር ነው። እነዚህን ከጨመርናቸው ነገሩ ምን ያህል የጣኦት አምልኮ ውስጥ የሚያስገባ የእግዚአብሔርንም ቅናት የሚያነሳሳ እንደሆነ መገመት አያስቸግርም።

  1. የሞቱ ወይም የተነጠቁ አማኞች በሰማይ ሆነው ስለኛ ሊጸልዩ ይችላሉ?

በጣም ግልጽ ባይሆንም አማኞች ወደ ሰማይ ከሄዱም በኋላ እግዚያብሔር በገለጠላቸውና እነርሱም ምድር ላይ ሳሉ በነበራቸው እውቀት ተመስርተው ሊጸልዩ እንደሚችሉ ፍንጭ ከመጽሃፍ ቅዱስ ማግኘት ይቻል ይሆናል (ራዕ 6፥10)። ወደ እነርሱ መጸለይ ግን ጣኦት አምልኮ ውስጥ ሊያስገባን እንደሚችል ከላይ ለማሳየት ሞክሪያለሁ። እግዚአብሔር በራሱ ፈቃድና ተነሳሽነት እንደሙሴና ኤሊያስ ሊገልጣቸውና መልእክት ሊሰጣቸው ይችላል ይሁን እንጂ እነዚህን በምድር የሌሉ አማኞች ስም እየጠሩ ወደ እነርሱ መጸለይ ግን በእግዚአብሔር ፊት ከጣኦት አምልኮ በተጨማሪ በመናፍስት ጠሪነትም ሊያስጠይቀን ይችላል (1ሳሙ 28፥1 – 28) ብየ አስባለሁ። “አይ የሞቱ ቅዱሳን ስለእኛ ይጸልያሉ እንዲጸልዩልንም ደግሞ ወደነሱ ብንጸልይ ምንም ችግር የለውም” ከሚል እምነቱ ወይ ፍንክች የሚል ሰው ይኖር ይሆናል። ለዚህም ሰው በድጋሜ ማሳስብ የምወደው ከላይ በዝርዝር እንዳሳየሁት በህይወት ያሉ ይሁኑ የሌሉ የቅዱሳን የምልጃ ጸሎት የመዳን ቅድመ ሁኔታ ሊሆን እንደማይችልና የምልጃ ጸሎታቸውም ከእግዚአብሔር ጋር ለማስታረቅ ብቸኛ ብቃት ያለውን የክርስቶስን የምልጃ ስራ የሚተካ ሊሆን እንደማይችል ነው።

  1. መላእክትስ ስለእኛ ይጸልያሉ?

መላእክት የሚድኑትን አማኞች የሚረዱ መናፍስት ስለሆኑ እግዚያብሔር ባሳያቸውና በተልዕኳቸው በሚገጥማቸው ነገር ተመስርተው ሊጸልዩ ወይም ጌታን ሊጠይቁ ይችላሉ። በመጽሃፍ ቅዱስ እንደምናየውም ከተገለጡልን (ከተገለጡልን የሚለው ቃል ይሰመርበት) ጥያቄ ልንጠይቃቸው እንችላለን (ልክ በምድር ላይ ላሉ ቅዱሳን አማኞች የጸሎት ጥያቄያችንን በአካል ወይም በደብዳቤ ወይም በሌላ መንገድ እንደምናስታውቀው ማለት ነው)፣ እነርሱም ካወቁት ሊመልሱልን ካላወቁት በእኛ ቦታ ሆነው እግዚአብሔርን ሊጠይቁልን ይችላሉ (ዘካ 1፥7-15)። ነገር ግን በምናባችን እያሰብንና ለጌታ እንደምናደርገው በመንፈሳዊ ተመስጦ ሆነን ወደ መላእክት መጸለይ ከላይ በዘረዘርኳቸው ምክንያቶች መሰረት የእግዚአብሔርን ቦታ ለፍጡር መስጠት ስለሆነ በጌታ ፊት በጣኦት አምላኪነት ያስጠይቀናል ብየ አምናለሁ።

መደምደሚያ

ለጊዜው ከላይ ያቀረብኳቸውን የመከራከሪያ ነጥቦች ረስተን ወይም አሳማኝ እንዳልሆኑ ቆጥረን፣ ለመዳን (ለመዳን የሚለው ቃል ይሰመርብት) የቅድስት ማርያም ወይም የሌሎች ቅዱሳንና መላእክት አማላጅነት ያስፈልገናል ማለት ምንድን ነው ጉዳቱ ብለን እንጠይቅ ይሆናል። ለመዳን የሚያስፈልገን የክርስቶስ የአማላጅነት ስራ ብቻ እንደሆነ በግልጽ መጻሃፍ ቅዱስ ላይ መስፈሩን ስላሳየሁ ይህን ጥያቄ መጠየቅ “መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ጥለን የማያስተምረውን መከተል ምንድን ነው ጉዳቱ” ብሎ እንደመጠየቅ እቆጥረዋለሁ። ለመዳን የቅዱሳን በተለይም የቅድስት ማርያም አማላጅነት ያስፈልገናል የሚለውን ትምህርት ችላ ብለን የምናልፈው ተራ ልዩነት እንዳልሆነ ግን ባጭሩ በማብራራት ጽሁፌን ልደምድም። እንዳንድ ሰዎች “ያለማርያም አማልጅነት ዓለም አይድንም” ማለታቸውን ማሰቡ የነገሩን አሳሳቢነት ግልጽ ያደርገዋል። ለመዳን የቅድስት ማርያም ወይም የሌሎች ቅዱሳን አማኞች ወይም የቅዱሳን መላእክት አማላጅነት ያስፈልጋል ማለት ክርስቶስና የክርስቶስ ሞት በቂ አይደለም እንደማለት ይቆጠራል። ለዚህም ሐዋርያው ጳውሎስ ለመዳን ከክርስቶስ ሞት በተጨማሪ መገረዝ ያስፈልገናል ላሉ የገላትያ አማኞች የጻፈውን ደብዳቤ ማንበብ በቂ ነው – ገላ 5፥2 – 6 “እነሆ፥ እኔ ጳውሎስ እላችኋለሁ፦ ብትገረዙ ክርስቶስ ምንም አይጠቅማችሁም. . . በሕግ ልትጸድቁ የምትፈልጉ ከክርስቶስ ተለይታችሁ ከጸጋው ወድቃችኋል።” ይላል። ልክ በክርስቶስ መስቀል ላይ ግዝረትን መጨመር ክርስቶስን ጥቅም አልባ በማድረግ ከክርስቶስ ጸጋ እንደሚለይ ሁሉ በክርስቶስ መስቀል ላይ የቅዱሳንንና መላእክትን ምልጃ ለመዳን እንደ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጥ ክርስቶስን ጥቅም አልባ በማድረግ ከክርስቶስ ጸጋ ይለያል። ለመዳን የክርስቶስ ስራ ላይ ምንም መጨመር ስለማይቻል ነው ሐዋሪያው ጳውሎስ በፊልጵስዩስ 3፥8 – 9 ክርስቶስን አገኝ ዘንድ ያለኝን ጥሩ ነገር እንኳ እንደ ጉዳት ብሎም አንደ ጉድፍ እቆጥራለሁ የሚለው። እነዚህን የገላትያ አማኞች ከእግዚአብሔር ጋር መታረቂያው ብቸኛው መንገድ የክርስቶስ መስቀል እንደሆነ ሌላም መጨመር እንደማይቻል ሲያስጠነቅቃቸው እንዲህ ይላል – “ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን። አስቀድመን እንዳልን እንዲሁ አሁን ሁለተኛ እላለሁ፥ ከተቀበላችሁት የተለየውን ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን።” ገላ 1፥6 – 9። ወንጌል ሰውን ከእግዚአብሔር ለለየው ችግር “መፍትሄ ተግኝቷል፣ መፍትሄውም ራሱን ለሁሉ ቤዛ በመስጠት በእግዚአብሔርና በሰው መካከለኛ ሆኖ ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር የሚያስታርቀው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” ብሎ የሚያውጅ የምስራች ቃል ነው። ጌታ ኢየሱስ በያዘው ይህ መካከለኛ የመሆን ድርሻ ላይ ቅድስት ማርያምን ይሁን ሌላ ሰውን ወይም መልአክን መጨመር ሐዋርያቱ ከየትኛውም ጥንታዊ ቤተክርስቲያን መመስረት በፊት አስቀድመው ከሰበኩት ወንጌል የሚለይ መጤ “ወንጌል” ነው።

እግዚአብሔር ያክብራችሁ!

8 thoughts on “አማላጅ ማነው? ኢየሱስ አዳኝ ወይስ አማላጅ?

  1. አብርሃም ነብይ ስለሆነ ማለደ ፣ለጸሎትማ ሁሉም ማድረግ ይችላል ሁለቱ ይለኛሉ ፣ማማለድ ከተወሰኑ ሰወች ሙደረግ ነገር ነው ፣ጸሎት ከሁሉም ነው።

    ዘፍ 20 6 እግዚአብሔርም በሕልም አለው፦ ይህን በልብህ ቅንነት እንዳደረግህ እኔ አወቅሁ፥ እኔም ደግሞ በፊቴ ኃጢአትን እንዳትሠራ ከለከልሁህ፤ ስለዚህም ትነካት ዘንድ አልተውሁም።

    7 አሁንም የሰውዬውን ሚስት መልስ ነቢይ ነውና፥ ስለ አንተም ይጸልያል፥ ትድናለህም። ባትመልሳት ግን አንተ እንድትሞት ለአንተ የሆነውም ሁሉ እንዲሞት በእርግጥ እወቅ።

    ነቢይ ነውና ስለ አንተ ይጸልያል።

    ጸሎት ቢሆን እራሱ አቢሜሌክ ማድረግ ይችላል ።

    Like

    1. “አብርሃም ነብይ ስለሆነ ማለደ” ስትል፣ አብርሃም የምልጃ ጸሎት አቀረበ እግዚአብሔርም ሰማው ማለትህ ከሆነ ምንም ችግር የለብኝም። በጽሁፌ እንዳሳየሁት አንደኛው የማማለድ ትርጉም “ለሌላ ሰው መጸለይ” ማለት ስለሆነ። ጸሎት ደግሞ ይሰራል፣ ለውጥ ያመጣል። ይሁን እንጂ በዘፍ 20፥6 ላይ የጠቀስከው ክፍል በአንድ ወቅት አብርሃም በህይዎት በነበረበት ጊዜ፣ ሚስቱን በመውሰድ ለበደለው ንጉስ፣ እንደ እግዚአብሔር ትዕዛዝ ሚስቱን በመለሰለት ጊዜ ስላደረገው የይቅርታ (የምልጃ) ጸሎትና እግዚያብሔርም ንጉሱ የአብርሃምን ሚስት መመለሱንና ጸሎቱን ተከትሎ በሳራ ምክንያት ያመጣባቸውን መዓት እንዴት እንዳነሳላቸው የሚዘግብ ነው። ያ ማለት ግን አብርሃም የኢየሱስን ቦታ ተክቶ ንጉሱ አቢሜሌክ ላደረገው ሐጥያት ሁሉ ስርየት አስገኝቶ በእግዚአብሔር ፊት ቅዱስና ነውር የሌለው አድርጎ ያቀርበዋል ማለት አይደለም። ወይም ለዓለም ሁሉ ህዝብ የይቅርታ ጸሎት እያደረገ የዓለምን ሁሉ ሐጥያት ያስተሰርያል ማለት አይደለም። ወይም አብርሃምን በአካል አግኝተውት የማያውቁ ሰዎች ሁሉ ለሐጥያታቸው ይቅርታ ወደ አብርሃም ይጸልዩ ነበር እርሱም ያስተሰርይላቸው ነበር ማለት አይደለም። ወይም አብርሃም ከሞተና በገነት ከሆነ በኋላ፣ ሰዎች መጀመሪያ ጸሎት ወደ እርሱ በማድረስ ቀጥሎም እርሱ ስለእነርሱ ወደ እግዚአብሔር በመጸልይ ለሐጢያታቸው ይቅርታ ያስገኝላቸው ነበር ማለት አይደለም። አቢሜሌክ የወሰደው የአብርሃምን ሚስት ባይሆን ኖሮ የአብርሃም ጸሎት ባላስፈለገ ነበር። አቢሜሌክ የሚሰራው ሐጥያት የአብርሃምን ሚስት መውሰድ ብቻ እንደማይሆን መገመት አይከብድም፣ እግዚአብሔር ግን ስለ ሌሎች በደሎቹ አቢሜሌክን ወይም ሌሎች ሰዎችን ስርየትን እንዲያገኙ ወደ አብርሃም ሲልክ ፈጽሞ አናይም። ምክንያቱም አብርሃም እርሱ ተበዳይ ባልሆነበት ምክንያት ሁሉ የይቅርታ ጸሎት እያደረገ ሊያስተሰርይ ስልማይችል ነው። ይህ ቢሆን አምላክ ሰው መሆን ብሎም እስከመስቀል ሞት መዋረድ ባላስፈለገው። ሐዋሪያቱም “ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤” እያሉ ከሚሰብኩ “ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ ወደ አብርሃም ጸልዩ” እያሉ ቢስብኩ ለአይሁድ ይቀላቸው ነበር።

      መጽሃፍ ቅዱስ ኢየሱስን “ስለ እኛ የሚማልደው” ብሎ እንዲሁም “ስለእነርሱ ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራል” ብሎ ሲያስቀመጠው – ሰዎች የሃጥያታቸውን ስርየት የሚያገኙትና ያለኩነኔና ቅዱሳን ሆነው በእግዚአብሔር ፊት የሚቀርቡበት ብቸኛው መንገድ ኢየሱስ ነው ማለቱ ነው። ታዲያ የአብርሃም ለአቢሜሌክ ያቀረበው ጸሎት ከዚህ ከኢየሱስ ስራ ጋር የሚያፎካክረው ሆነ የሚያገናኘው ነገር የለም። የአብርሃም ጸሎት ኢየሱስ በማቴ 5፥24 “እንግዲህ መባህን በመሠዊያው ላይ ብታቀርብ፥ በዚያም ወንድምህ አንዳች በአንተ ላይ እንዳለው ብታስብ፥ በዚያ በመሠዊያው ፊት መባህን ትተህ ሂድ፥ አስቀድመህም ከወንድምህ ጋር ታረቅ፥ በኋላም መጥተህ መባህን አቅርብ።” ብሎ ካለው የሚነጻጸር ነው። የበደልከው ወንድምህ ይቅር ብሎህ ሳይፈታህ መባህን እግዚአብሔር ሊቀበልህ እንደማይችል እንዲሁ አቢሜሌክም ከበደሉ የተነሳ ከመጣበት መዓት፣ የወሰዳትን ሚስት ሳይመልስና ከበደለው ከአብርሃም የይቅርታን ጸሎት ሳያገኝ መዓቱ ሊነሳለት አይችልም።

      “ነብይ ነውና” የሚለው ቃል “ነብይ ነውና ሚስቱን መልስ” ለማለት እንጂ፣ አንተ እያልክ ባልህበት መንፈስ “ነብይ ስለሆነ አማላጅ ነው” ማለቱ አይደለም። ለዚህም ማስረጃው “አሁንም የሰውዬውን ሚስት መልስ ነቢይ ነውና” ብሎ ነጠላ ሰረዝ ካስቀመጠ በኋላ ነው “ሰለ አንተም ይጸልያል” የሚለው።

      Like

  2. ጌታ ይባርካችሁ ።ስለ ደህንነት ጥያቄ ነበረኝ ሰው ዳግም ከተወለደ በኋላ ደህንነቱን በምን ሊያጣ ይችላል ?

    Liked by 1 person

    1. ምህረታብ፣ እንደዚህ ነው፣ በዚህ ሁኔታ ነው፣ ይህ ሲኖን ነው ብሎ መደምደም ለኔ በጣም ከባድ ነው። ነገር ግን ደንነትን ጸንቶና ነቅቶ በመጠበቅ ጉዳይ ሁልጊዜም አእምሮየ ውስጥ ያለው ዕብራዊያን 10:19-31 ያለው ክፍል ነው። እንድታነበው ልጋብዝህ

      19-20 እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ በመረቀልን በአዲስና በሕያው መንገድ ወደ ቅድስት በኢየሱስ ደም በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል እንድንገባ ድፍረት ስላለን፥
      21 በእግዚአብሔርም ቤት ላይ የሆነ ታላቅ ካህን ስላለን፥
      22 ከክፉ ሕሊና ለመንጻት ልባችንን ተረጭተን ሰውነታችንንም በጥሩ ውኃ ታጥበን በተረዳንበት እምነት በቅን ልብ እንቅረብ፤
      23 የተስፋን ቃል የሰጠው የታመነ ነውና እንዳይነቃነቅ የተስፋችንን ምስክርነት እንጠብቅ፤
      24 ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤
      25 በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው፥ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ።
      26 የእውነትን እውቀት ከተቀበልን በኋላ ወደን ኃጢአት ብናደርግ ከእንግዲህ ወዲህ ስለ ኃጢአት መሥዋዕት አይቀርልንምና፥
      27 የሚያስፈራ ግን የፍርድ መጠበቅ ተቃዋሚዎችንም ሊበላ ያለው የእሳት ብርታት አለ።
      28 የሙሴን ሕግ የናቀ ሰው ሁለት ወይም ሦስት ቢመሰክሩበት ያለ ርኅራኄ ይሞታል፤
      29 የእግዚአብሔርን ልጅ የረገጠ ያንንም የተቀደሰበትን የኪዳኑን ደም እንደ ርኵስ ነገር የቆጠረ የጸጋውንም መንፈስ ያክፋፋ፥ እንዴት ይልቅ የሚብስ ቅጣት የሚገባው ይመስላችኋል?
      30 በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ ያለውን እናውቃለንና፤ ደግሞም፦ ጌታ በሕዝቡ ይፈርዳል።
      31 በሕያው እግዚአብሔር እጅ መውደቅ የሚያስፈራ ነው።
      32-33 ነገር ግን ግማሽ በነቀፋና በጭንቅ እንደ መጫወቻ ስለ ሆናችሁ ግማሽም እንዲህ ካሉት ጋር ስለ ተካፈላችሁ፥ ብርሃን ከበራላችሁ በኋላ መከራ በሆነበት በትልቅ ተጋድሎ የጸናችሁበትን የቀደመውን ዘመን አስቡ።
      34 የሚበልጥና ለዘወትር የሚኖር ገንዘብ በሰማይ ራሳችሁ እንዳላችሁ አውቃችሁ፥ በእስራቴ ራራችሁልኝ የገንዘባችሁንም ንጥቂያ በደስታ ተቀበላችሁ።
      35 እንግዲህ ታላቅ ብድራት ያለውን ድፍረታችሁን አትጣሉ።
      36 የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋልና።
      37 ገና በጣም ጥቂት ጊዜ ነው፥ ሊመጣ ያለውም ይመጣል አይዘገይምም፤
      38 ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል ወደ ኋላም ቢያፈገፍግ፥ ነፍሴ በእርሱ ደስ አይላትም።
      39 እኛ ግን ነፍሳቸውን ሊያድኑ ከሚያምኑቱ ነን እንጂ ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉ አይደለንም።

      Like

  3. please ከቻልክ ቶሎ መልስልኝ ፡፡

    የሮሜ 8:26,27 መማለድ ብሎ የሚያወራው ምንድነው ፡ከ ቁጥር 34 ጋር አብሮ ይሄዳል ወይ፡፡

    Like

  4. አንዴት ያለ ድንቅ መልዕክት ነው!! ኢየሱስ እውነትም አማላጅ ነው!! ሊታረቅ ያልቻለውን ሰው መካከለኛ ሆኖ በስጋው ሞት አስታርቋል!!

    Like

Leave a comment